AMN- ግንቦት 11/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የቆሻሻ መጣያና ለአይን ለማየትም ሆነ ለአፍንጫ የሚረብሹ የነበሩ አካባቢዎች መጽዳት እና መልማት መቻላቸው ለነዋሪዎች ምቾትን ፈጥረዋል ሲሉ “አዲስ አበባን እንደ አዲስ” የተሰኘው መጽሐፍ ፀኃፊዎች ገለጹ፡፡
የከተማዋን ፈጣን እድገት ከታዘቡ መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሂርጶ ቁምቢ (ዶ/ር) እና እንግሊዛዊው ጸኃፊ ስሞን ሊ (ፕ/ር) ፤ መጽሐፉን ለመጻፍ የከተማዋ ለውጥ መነሻ እንደሆናቸው በማንሳት በመጽሐፉም ከአዲስ አበባ ሊወሰድ የሚችለውን ተሞክሮ ማካተታቸውን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል፡፡
አዲስ አበባ ወደ መልካም ገጽታ መቀየሯን፣ ከተማዋ በየጊዜው ለውጥ እያሳየች መሆኑን የአዲስ አበባን እንደ አዲስ መጽሐፍ ፀኃፊ ሂርጶ ቁምቢ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ጥሩ የሚባለው የቦሌ ጎዳና እንኳን በጣም መጥፎ ሽታ ነበር ያሉት ሂርጶ ቁምቢ (ዶ/ር)፤ ከወራት በኋላ ድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ግን ሙሉ በሙሉ ወደ መልካም ገጽታ ተቀይሯል ብለዋል።

ለግል ጉዳይ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የከተማዋን ለውጥ መመልከት እንደቻሉ ጠቅሰው፣ በአዲስ አበባ የተጀመሩ ግንባታዎች በአጭር ጊዜ ሲያልቁ መመልከታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በዚህም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ይህንን ጉዳይ ማጥናት አለብኝ በማለት መጽሐፉን ወደ ማዘጋጀት መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡
እንግሊዛዊው ጸሐፊ ስሞን ሊ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ሰዎች ስለ አዲሱ የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ ስለ ሙዚየሙና ስለመሳሰሉት ግንዛቤው እንዳላቸው ገልጸው መጽሐፉን ሲያነቡ ደግሞ ከጎዳና ላይ ስለተነሱ ሴቶችና ሌሎች የተከናወኑ ልማቶች ይረዳሉ ብለዋል፡፡
እኛ ለአዲስ አበባ ልንሰጣት ከምንችለው በላይ አዲስ አበባ ብዙ ትምህርቶችን መልሳ ልትሰጠን ትችላለች፣ አዲስ አበባ ያስመዘገበችው የአጭር ጊዜ ለውጥ ከሌሎች የዓለም ከተሞች ተርታ የሚያሰልፋት መሆኑንም ባደረግነው ጥናት መረዳት ችለናልም ነው ያሉት፡፡

እንዲህ አይነት ስኬት ለማስመዝገብ ራዕይና የአመራር ቁርጠኝነት እንዲሁም ቅንጅት ወሳኝ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡ ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችም በትትብር እየሰሩ መሆኑን በማንሳት ሕዝቡም የልማቱ አጋር እንዲሆን ከተማ አስተዳደሩ መስራቱን ተረድቻለሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ከቀጠለች እና ኢኮኖሚያዊ እድገቷም ከቀጠለ አዲስ አበባ የተሻለች ከተማ ትሆናለች ሲሉም ፀኃፊዎቹ ገልጸዋል።
አዲስ አበባን እንደ አዲስ የተሰኘው መጽሐፍ በከተማዋ ባለፉት ጥቂት አመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎችን በስፋት የቃኘ ሲሆን የከተማዋን ፈጣን እድገት ሰንዶ ከማስቀመጥ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ምሁራኑ በከተማዋ የተመለከቱትን ፈጣን እድገት ተመልክተው “The Remark of Addis Ababa” ወይም “አዲስ አበባን እንደ አዲስ” የተሰኘውን መጽሐፍ በማዘጋጀት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ማስመረቃቸው ይታወሳል፡፡
የሻምበል ምህረት