AMN- ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ከ2014 እስከ 2018 የትምህርት ዘመን ለተከታታይ አምስት ዓመታት የተከናወኑ የትምህርት ስራዎች ግምገማዊ ስልጠና መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የተሻለ አስተሳሰብ ያለውና በእውቀት የዳበረ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
የተማሪዎችን ውጤት ማሳደግ፣ የተማሪዎችን ስነ ምግባር ማሻሻል፣ የተሻለ የትምህርት ከባቢ መፍጠር እና መሰል የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል።

የተጀመሩና ውጤት ያሳዩ ተግባራት ነገን የተሻለ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ በማሰብ እንዲሁም ጠንካራ አመራርነት በመስጠት ለነገ ሀገርና ትውልድ መትጋት ይጠበቃል ሲሉ አሳስበዋል።
ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) አክለውም፤ በእውቀት የዳበረና በሙሉ ስብዕና የታነፀ ትውልድ መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አበራ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በትምህርት ተደራሽነትና ጥራት፣ በተማሪዎች ምገባ ፣ በትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ላይ እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ግንባታና ማስፋፊያ ላይ የተሰሩ ስራዎች ለስኬቱ መሰረት ናቸው ብለዋል።
የግምገማ መደረኩ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑም ተመላክቷል።
በንጉሱ በቃሉ