አዲስ አበባን 24 ሰዓታት የምትሰራ ከተማ ማድረግ ተችሏል

AMN- ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ የ24 ሰዓታት የሥራ እንቅስቃሴ የምታደርግ ከተማ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰብስብ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

ባለሥልጣኑ ጳጉሜን 2ን “የማንሰራራት ቀን” በማስመልከት ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን የሥራ አፈጻጸሞች በኤግዚቢሽን እያሳየ ይገኛል። ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት አስተያየት፤ ከተማዋን በመብራት አገልግሎት በታማኝነት ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑት ሥራዎች አዲስ አበባ በየዘርፉ እያሳየች ያለውን ማንሰራራት አመላካች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተቋሙ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ የመብራት መሠረተ ልማቶችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ሰብስብ ሁሴን (ዶ/ር)፤ በየትኛውም ሥፍራ ችግር ቢፈጠር በአፋጣኝ የጥገና ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር በመዘርጋቱ ውጤታማ መሆን መቻሉን አስረድተዋል።

እንዲሁም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም በማልማት ለዘርፉ ዕድገትና መዘመን ጠንካራ መሠረት መጣሉን ጠቁመዋል።

በተለይም የመንገድ ላይ መብራቶችን በስፋት፣ በጥራትና በሁሉም አካባቢዎች በመትከል የከተማዋን ገጽታ የሚመጥን አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማህበረሰቡ እነዚህን መሠረተ ልማቶች በባለቤትነት ስሜትና በኃላፊነት ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ኤግዚቢሽኑን የጎበኙ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ በከተማዋ የተከናወኑት ሰፊ የመብራት መሠረተ ልማት ሥራዎች የሌሊት እንቅስቃሴዎችን ሰላማዊ ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን የምሽት ገጽታ በእጅጉ እንዳሳመሩት ተናግረዋል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review