ጦርነትን የመረጠው ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን እስከ ዛሬ ድረስ ከጦርነት ምን አተረፈ?

You are currently viewing ጦርነትን የመረጠው ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን እስከ ዛሬ ድረስ ከጦርነት ምን አተረፈ?

AMN ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም

ጦርነት አውዳሚ ነው፤ ለዚህ ደግሞ እንደ ሶሪያ፤ የመን፤ ሱዳን፤ ሊቢያ፤ ዩክሬን እና ሌሎች ጦርነት ያወደማቸውን የአፍሪካና የዓለም ሀገራትን በምሳሌትነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም ከዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ በየዘመናቱ የተለያዩ የጦርነት ታሪኮችን ማሳለፏን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከቅኝ ገዢዎች ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ለጥቁር ህዝቦች አርአያ የሚሆን ገድል የፈጸሙ ቢሆኑም፣ በሀገር ውስጥ በተፈጠሩ የፖለቲካ አዙሪቶች ምክንያትም ትልቅ መስዋዕትነት እስከመክፈል ደርሰዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት በፊት ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በከፈተው ጦርነት ተመሳሳይ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ይህ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መቋጫ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

በየዘመናቱ የተከሰቱ ጦርነቶችና ግጭቶች ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት የሚያስከትሉ፣ የሀገርን ልማትና ሰላም እንዲሁም የመጪውን ትውልድ መጻኢ እድል የሚያደናቅፉ ከሆነ ጦርነቶቹን ቀድሞ መከላከልና ማስቆም አይቻልም ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ይፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይህንኑ የጦርነት አዙሪት አስመልክቶ በመደመር መንግስት መጽሃፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ማሸነፍና መሸነፍ የጦርነት ባሕርይ ቢሆንም፣ ጦርነት የሚያስከትለውን ውድመት አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር ምን ያህሉ በድንገት ደረሰብን? ምን ያህሉንስ በድርድር ለመፍታት ሞከርን? ሌላ መፍትሄስ የለም ነበር ወይ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ሕዝቡ በጦርነት አዙሪት ልጆቹን የሚገብርበት እና ሀገሪቱም ወጣቶቿን በጦርነት አጥታ የምትሰበርበት ምክንያት ምንድነው ሲሉ ከመጠየቅ አልፈው ይህ ጉዳይ ምርመራ እንደሚፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሀገሪቱ በተደጋጋሚ ወደ ጦርነት የምትገባበት ምክንያት ራሱን የቻለ ምርመራና ምላሽ የሚፈልግ ቢሆንም፣ ወደ ጦርነት የሚወስዱ ልዩነቶችን በምክክር ቀርፎ የሰውን ሕይወት ከሞት፣ ንብረትን ከውድመት መታደግ ግን አማራጭ የሌለው ትልቅ መፍትሄ ነው፡፡

በሚያግባቡም ሆነ መግባባት በማያስችሉ ልዩነቶች ምክንያት ሁል ጊዜ ጦር አንስቶ መሸፈት፤ መገዳደልና ንብረት ማጥፋት መጨረሻው ኪሳራ እንጂ አንድም ትርፍ እንደሌለው የተገነዘቡት ኢትዮጵያውያን ከዚህ የፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት እና ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በንግግርና በምክክር ለመፍታት የመጀመሪያውን ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

መላው ኢትዮጵያዊያ የጦርና የጦርነትን ምዕራፎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ዘግተው ለመጪው ትውልድ የለማችና ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለመገንባት የምክክር ጉዞ እያደረጉ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ጽንፈኛው የሕወሃት ቡድን ግን ከሻዕቢያና ከሌሎች ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ካላቸው ቡድኖች ጋር በማበር ዛሬም ሌላ ጦርነት ለመጀመር ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣ ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን እያደረገ ያለውን አፈናና የጦርነት ዝግጅት እየተቃወሙ ባለበት በአሁኑ ወቅት እንኳ ጽንፈኛው ቡድን ግን ለሁሉም ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ ጦርነት ነው የሚል አቋም ይዟል፡፡

ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን መንግስትን ጨምሮ የትግራይ ክልል ህዝብ እና መላው ኢትዮጵያዊያን እያቀረቡት ያለውን የሰላም ጥሪ ወደጎን ትቶ ዳግም ጦርነትን የመረጠበት ምክንያት ምን ይሆን?

የዚህ ጦርነት ሰለባ የሚሆኑትስ አዲስ አበባን ጨምሮ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና በተቀረው ዓለም በምቹ ሁኔታ ውስጥ ቁጭ ብለዉ የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙት የህገ-ወጡ ህወሃት ቡድን ቤተሰቦች ናቸው ወይስ ጦርነት የመረራቸው የትግራይ ልጆች?

ጸንፈኛው እና ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ጦርነት አንፈልግም ብለው ክልሉን ለቀው የሚሰደዱ የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ አፍሶ ወደ ጦር ሜዳ በመላክ የሚያገኘው የጦር ሜዳ እና የፖለቲካ ድልስ ምን ይሆን?

ከትናንትናው ስህተት መማር አቅቷቸው ዛሬም ሌላ ጦርነት ለመቀስቀስ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግሮችን እና የጦርነት ቅስቀሳዎችን የሚያደርጉት የህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን አክቲቪስቶችና ቅጥረኞቻቸው የገዛ ወገኖቻቸውን በጦርነት በመማገድና የትግራይን ክልል የጦርነት ማዕከል በማድረግ የሚያገኙት ትርፍ ምን ይሆን?

ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን የቀረቡለትን የሰላም አማራጮች በሙሉ አልቀበልም ብሎ ዳግም ጦርነት ቢጀምር፣ ከዚህ ጦርነት ከሻዕቢያና ሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በስተቀር የትኛው ኢትዮጵያዊ ከግጭት ያተርፍ ይሆን?

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review