AMN- ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አሊ አሕመድ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ዋነኛ ዓላማ ታዳጊዎችን ለማነቃቃትና የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ዕድገት ለመደገፍ እንደሆነ ገለጸ።
አሊ አሕመድ ለኤ ኤም ኤን በሰጠው ቃለ-ምልልስ፤ ኢትዮጵያ ለእግር ኳስ የጠለቀ ፍቅርና ስሜት ያለው ማኅበረሰብ ያላት ሀገር በመሆኗ በዓለም ዋንጫ መሰል ትልልቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ለመወዳደር የሚያስችል አቅም እንዳላት ተናግሯል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለውን ሁኔታ ሲያብራራም፤ እንደ አለመታደል ሆኖ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልጫወት አልቻልኩም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ሆና ማየት ለእኔ በዓለም ዋንጫ ላይ እንደመጫወት ያህል ትልቅ ስሜት ይፈጥርብኛል ብሏል።

አክሎም የእግር ኳስ ሕልማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ታዳጊዎችን ማየት እጅግ የሚያስደስት እና ተስፋ ሰጪ መሆኑን በመጥቀስ የሀገሪቱን እግር ኳስ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከመዋቅር ጀምሮ ዘመናዊ አሰራርን መዘርጋት እንዲሁም በሀገር ውስጥ መጠነ-ሰፊ የታዳጊዎች ስልጠና ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝቧል።
አሊ አህመድ፤ ወላጆቹ ለብዙ ዓመታት በኖሩበት ሀገር በመገኘቱ ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት የገለጸ ሲሆን ይህ ጉዞ ከዚህ በፊት ካቀደው የእረፍት ጊዜ በላይ ትርጉም ያለው አጋጣሚ እንደሆነለት አረጋግጧል።
በወርቅነህ አቢዮ