AMN- ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

ባለፉት አምስት አመታት በትምህርት ልማት ሥራው የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ይበልጥ እንዲሻሻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም የተከናወኑ ተግባራትን እና የ2019 ዓ.ም እቅድን መሰረት አድርጎ ሲያካሂድ የነበረዉን ግምገማዊ ስልጠና አጠኗቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ የትምህርት አመራሩን እና ወላጆችን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት አቅም በአግባቡ በመጠቀም የትምህርት ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻል ያከናወናቸው ተግባራት በተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

የተመዘገበው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ በቀረበዉ ሰነድ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ባለፉት አምስት አመታት የተማሪዎች ውጤት መሻሻል ላይ ለውጥ መታየቱን ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡
የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ ከማድረግ ባለፈ ውጤታቸው እንዲሻሻል ማስቻሉንም ነው ተሳታፊዎቹ የገለጹት፡፡
ከሙያ ትምህርት ጋር ተያይዞ የባለሙያ እጥረት መኖሩንና የፈረቃ ትምህርት እንዲቀር የሚደረገው ጥረት አሁንም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚገኙ አዋኪ ድርጊቶችን መቆጣጠር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በትምህርት ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
በዝናሽ ሞዲ