ከሕዝብ ድምጽ እስከ ምክክር መድረክ – የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ

You are currently viewing ከሕዝብ ድምጽ እስከ ምክክር መድረክ – የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ

AMN – መስከረም 5/2019 ዓ.ም

ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ቀን በሚከበርበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በማጠናቀቅ እና ስር የሰደዱ ሀገራዊ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የጀመረችውን ሰላማዊ ሂደት አጠናክራ ቀጥላለች።

እነዚህ ሁለት ታሪካዊ ኹነቶች የዴሞክራሲ ባህልና ትግበራ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የጸና መሠረት ይዘው እየጎለበቱ መምጣታቸውን በተግባር አሳይተዋል።

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆነውን ሕዝባዊ ውክልና ለማረጋገጥ በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመምረጥ በመመዝገብ ከፍተኛ የዴሞክራሲ ተሳትፎ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን ጠብቆ አሰራሩን አካታች በማድረጉም፤ ተማሪዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ተፈናቃዮች የዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

ዜጎች በማለዳ ወጥተው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በትዕግስት በመሰለፍ ድምጻቸውን መስጠታቸው፣ እንዲሁም ተመራጮች እና ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት በሰላማዊ መንገድ መቀበላቸው በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የሕዝብ ድምጽ የበላይነት መረጋገጡን ያበስራል።

ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ ለዴሞክራሲያዊ ሂደቱ መጠናከር እንደ አንድ ትልቅ እርምጃ አድንቀውታል።

ከጠቅላላ ምርጫው ባሻገር ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዋን ያጎለበተችበት ሌላኛው ማሳያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤን በስኬት ማካሄዷ ነው።

ዴሞክራሲ በድምጽ መስጠት ብቻ ሳይወሰን በዜጎች ቀጣይነት ያለው የውይይትና የምክክር ባህል ጭምር የሚጎለብት መሆኑን በመገንዘብ፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል አደረጃጀቶች የተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ መክረዋል።

የ130 ሚሊዮን ዜጎችን ድምጽ ያንጸባረቀው ይህ ጉባኤ የፖለቲካና የማህበራዊ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ የመፍታት የዴሞክራሲ መርህን መሠረት ያደረገ ነው።

በምርጫው ሂደት የታየው ንቁ የዜጎች ተሳትፎ እና በምክክር ጉባኤው የተንጸባረቀው የውይይት ባህል፣ ኢትዮጵያ ወደፊት የምትገነባው በሕዝብ ድምጽ እና በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ ብቻ መሆኑን ያረጋገጡ ናቸው።

በመሆኑም እነዚህ ሁለት ሀገራዊ ኹነቶች የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ መሠረት ከማጠናከራቸው ባለፈ ለቀጣናው ሀገራት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መልካም ተምሳሌት ሆነው ያገለግላሉ።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review