ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል የጀመራቸው ተጨባጭ ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ አደም ፋራህ

AMN ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

ብልፅግና ፓርቲ በፓርቲና በመንግሥት የተቀናጀ አመራር የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት፣ የገበያ መረጋጋትን ለማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የጀመራቸው ተጨባጭ ሥራዎች በሕዝብ ሕይወት ላይ የሚታዩ ለውጦችን እያስመዘገቡ መሆናቸውን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ይህንን የተናገሩት በ2018 በጀት ዓመት በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ማረጋጋትና በኑሮ ውድነት ቅነሳ ዙሪያ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን የገመገመ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ነው።

እንደ ገለጻቸው፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገበያ መረጋጋትና የኑሮ ውድነት ቅነሳ የመንግሥት መደበኛ ፕሮግራሞች ብቻ ሳይሆኑ የፓርቲው ዋና ዋና የፖለቲካ ተልዕኮዎች በመሆናቸው በሁሉም የአመራር እርከኖች በንቅናቄ ተመርተዋል። ይህም ከዕቅድ አፈጻጸም ባለፈ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን እንዲመዘገቡ ማስቻሉን አመልክተዋል።

በሁሉም ክልሎች በስራ ዕድል ፈጠራና በኑሮ ውድነት ቅነሳ ዘርፎች የሚታዩ መሻሻሎች መመዝገባቸውን የገለጹት አቶ አደም፤ ያለውን የሀገሪቱን አቅምና የሕዝቡን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ግን ከዚህ በላይ ሊሠራ የሚገባ ብዙ ሥራ እንዳለ አስገንዝበዋል።

“ሁለቱንም የትኩረት መስኮች በሕዝብ ንቅናቄ በመምራታችን ጉዳዩን እስከ ቀበሌ ድረስ የአመራር አጀንዳ ማድረግ ችለናል፤ ይህም ተጨባጭ ለውጥ አስገኝቷል። አሁን ያለውን ጅምር ማጠናከርና ወደ ከፍተኛ ውጤት ማሸጋገር ይጠበቃል” ብለዋል።

አቶ አደም የፓርቲ አደረጃጀቶችና አባላት በዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ በማሳሰብ፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል። የእያንዳንዱን አካባቢ የልማት አቅምና የገበያ እውነታ መሠረት በማድረግ ለሕዝቡ ቀጥተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ምርቶችን በመለየት የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል የቀጣይ ትኩረት መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

እንዲሁም የሕዝብ ባለቤትነትንና የተደራጀ ተሳትፎን በማጠናከር፣ ከአሰራር፣ ከአመለካከትና ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ማነቆዎችን በመፍታት ሥራዎቹን ዘላቂ፣ ተቋማዊና ሥርዓታዊ በሆነ አግባብ ማስቀጠል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

አቶ አደም በማጠቃለያቸው፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዶች በተሻለ አፈጻጸም እንዲተገበሩ ሁሉም የፓርቲ መዋቅሮችና የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት፣ በተጠያቂነትና በውጤት ተኮር አሰራር ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ፣ በቀጣይ የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ የበለጠ ለማሻሻል የሚያስችሉ የትኩረት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁን ከፓርቲዉ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review