AMN -ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም

ሀገር ማለት የዜጎች የጋራ መኖሪያ ብቻ ሳትሆን የትውልዶች ቅርስ፣ የክብር ማማ እና የነገ ተስፋ ነች። ይህንን የጋራ ቤት አስተማማኝና ጽኑ አድርጎ ለማቆየት አገራዊ ፅናት ወሳኝ ሚና አለው።
ፅናት ማለት በፈተና ጊዜ ላለመንበርከክ፣ በችግር ውስጥ አብሮ ለመቆም እና ለጋራ ዓላማ ፀንቶ የመቆም ብሔራዊ ኃይል ነው።
ሰላም የሌለበት ማህበረሰብ ሁለንተናዊ እድገትን ማሰብ ፈጽሞ አይችልም። ልማት፣ ትምህርት፣ጤና እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሚከናወኑት በሰላም ጥላ ሥር ብቻ ነው።

ጠንካራ አገራዊ ፅናት ያላቸው ሕዝቦች ማንኛውም ፈተና ሲገጥማቸው በአንድነት በመቆም አገራቸውን ከውጭም ሆነ ከውስጥ አደጋዎች ይታደጋሉ።
ልዩነቶችን እንደ ውበት በመቁጠር በጋራ እሴቶች ላይ መጽናት የሰላም ዋስትና ነው። አገራዊ ፅናት የዜጎችን ሁለንተናዊ ሁነታ የሚያፋጥን ኃይል ነው።
ዜጎች በሀገር ውስጥ ሀብት ላይ ያላቸው እምነት እና የልማት ተሳትፎ ሲጠናከር ኢኮኖሚው ከውጭ ጫናዎች ይላቀቃል። ጠንካራ አገር ለመገንባት የሚደረግ ትግል ዜጎች በሀገራቸው ላይ ያላቸውን ፍቅር እና የባለቤትነት ስሜት ከፍ ያደርገዋል።
አገራዊ ፅናት የሚገነባው በአንድ ሌሊት ሳይሆን በጋራ ጥረት ነው። ይህም ከማንነት በፊት አገራዊነትን በማስቀደም፣ ወጣቱ ትውልድ ስለ ሀገሩ ታሪክ እና እሴቶች በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣ የሀገር ሀብት በፍትሃዊነት ሲከፋፈል የዜጎች አገራዊ ፍቅር እጅግ ይጠነክራል።
የአንድ አገር ሰላም እና እድገት የሚለካው በሕዝቧ ጽናት ልክ ነው። ዛሬ የምንዘራው የፅናት፣ የፍቅር እና የአብሮነት ዘር ለነገዋ የበለጸገች እና ጸጥታ የሰፈነባት አገር መሠረት ነው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ