ኢትዮጵያ የጸናችበት ሌላኛው ብስለት

AMN-ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም

የሀገርን ሉዓላዊነት ፣ የግዛት አንድነትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጥቃቶች በጀግንነትና በጽናት የሚጠብቁት የጸጥታና ደኅንነት ተቋሟት ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈዋል።

ወታደራዊ አቅማቸውን ከዘመናዊ የዲጂታል ደኅንነት ጋር በማቀናጀት የሀገርን ጋሻ ያጠናከሩት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፤ ዳር ድንበሯ የታፈረና ሕዝቧ በሰላም የሚኖርባት ሀገር ትሆን ዘንድ ሌት ተቀን ይተጋሉ።

ከዚህም ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት የሰላም አየር እንዲነፍስ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን በማሰማራት ለቀጣናው ሰላም ያላቸው አበርክቶ የላቀ ነው። በዚህ አኩሪ ገድል ታጅቦ ጳጉሜን 3 “የጽናት ቀን” ሲከበር የሀገሪቱ ጀግኖች በልዩ ክብር እየታሰቡ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ጽናታቸውን በጦር ሜዳና በዲጂታል ደኅንነት ብቻ ሳይሆን በሰለጠነው የምክክር ጠረጴዛ ላይ ጭምር ማረጋገጣቸው የጽናት ቀን አከባበር ልዩ ያደርገዋል።

ጠንካራ ሀገር መገንቢያው ሥልጡን መንገድ ምክክር መሆኑን የተገነዘቡት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ታሪካዊውን የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በስኬት አከናውነዋል።

የውስጥ አንድነቷ የተጠናከረች፣ ልዩነቶቿን በምክክር የፈታች እና በጋራ ትልሞች ላይ በማተኮር በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባች ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆን ዘንድ፤ መስተካከል አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ በራሳቸው መሪነትና አስተባባሪነት የመረጧቸውን ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች መሠረት በማድረግ በስፋት መክረዋል።

አካታች በሆነ መንገድ የተወከሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በመዲናችን አዲስ አበባ ባካሄዱት ሁሉን አቀፍ ውይይት የ130 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ድምጽ አንጸባርቀዋል።

ተመካካሪዎቹ አንዱ የሌላውን ሀሳብ በማክበር፣ በማዳመጥና “የእርሱ ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው” በማለት መተሳሰብንና አብሮነትን አጉልተው በማሳየት ኢትዮጵያ በምክክር እንድትጸና አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ይህ ምክክር ስኬታማ እንዳይሆን ሐሰተኛና አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት ውዝግብ ለመፍጠር የሞከሩ ቢሆንም የኮሚሽኑ ተቋማዊ ገለልተኛነቱን በመጠበቁ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ጽኑ አንድነት የጠላት ሴራ በመክሸፉ ኢትዮጵያ ዳግም እንድታሸንፍ አስችሏል።

ልዩነትን በምክክር የመፍታት ልምምድ ከሀገር አልፎ ለቀጣናውም ሀገራት ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው። የጸጥታ ኃይሎች በድንበር ዜጎች ደግሞ በሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር ያላቸውን ጽናትና ቁርጠኝነት አሳይተዋል፡፡

በትዝታ መንግሥቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review