በውይይትና በምክክር ችግሮችንና ልዩነቶችን መፍታት የስልጣኔ ምልክት ነዉ

AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ለዘመናት ስር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ ሀገሪቱን ወደ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ጉዞ ላይ ይገኛል።

ኮሚሽኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም በሕዝቦች መካከል በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከአጀንዳ ማሰባሰብ በመሻገር ወደ ዋናው የምክክር ምዕራፍ የተሸጋገረው ይህ ታሪካዊ ሂደት፤ ለተለያዩ አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮችን ከስር መሰረታቸው ለመፍታትና በህዝቦች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ሰፊ መደላድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

በዚሁ ታሪካዊ የምክክር መድረክ ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮች፣ እንዲሁም ለሰላም ቅድሚያ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የታጠቁ ኃይሎች በንቃት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ኮሚሽኑ፤ አሁንም በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ኃይሎችና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር ሂደቱ ቢጀመርም እንኳ መጥተው እንዲሳተፉ እና የሰላሙ አካል እንዲሆኑ ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ከጦርነት የሚገኝ አንዳችም ትርፍ እንደሌለና በውይይትና በምክክር ችግሮችን መፍታት የስልጣኔ የመጀመሪያው መርህ ሀሁ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ሁለት ዓመት ከመዋጋት ሃያ ዓመት መወያየት ይሻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁለት ዓመት ስንዋጋ ብዙ እናወድማለን፤ ብዙ ንብረትና ሕይወት እናጣለን፤ ውስጣችን ይሞታል፣ የመፍጠር አቅማችንም ይዳከማል ብለዋል።

ሃያ ዓመት ስንወያይ ግን የፈለግነውና የተመኘነው ነገር በአጭር ጊዜ ያልተከወነ ቢሆን እንኳ፣ ሰው ሳንጎዳና ንብረት ሳናወድም ለመማር እድል የሚሰጥ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ሊነቁ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በምክክር የጸናችና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ ተሳታፊዎች በቡድን ተከፋፍለው ምክክራቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ በሚመካከሩባቸው አጀንዳዎች ላይ በርካታ ገንቢ ምልከታዎችን እያቀረቡ እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review