ግብፅ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የምታቀርበው ተቃውሞ ከግድቡ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም

AMN- ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ግብፅ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የምታቀርበው ተቃውሞ ከግድቡ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ይልቁንም የዓባይ ወንዝ ውሃ እንዴት ሊተዳደር እንደሚገባ በሚመለከት መሠረታዊ የአመለካከት ልዩነት ነው።

ለብዙ ዓመታት ግብፅ ሕጋዊ አቋሟን እ.አ.አ በ1929 በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመው የአንግሎ-ግብፅ ስምምነት እና እ.አ.አ በ1959 በግብፅና በሱዳን መካከል በተፈረመው የዓባይ ውሃ ስምምነት ላይ መስርታለች።

ሁለቱ ስምምነቶች አብዛኛውን የዓባይ ውሃ ለግብፅና ለሱዳን ብቻ በመመደብ ሌሎችን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሂደቱ ውጭ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በሁለቱም ስምምነቶች ተሳታፊ ስላልነበረች ያለ ኢትዮጵያ ፈቃድና ተሳትፎ በተደረጉ ስምምነቶች በሕግም ሆነ በሥነ-ምግባር እንደማትገዛ ታስረዳለች።

ከኢትዮጵያ እይታ አንጻር በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ ስምምነቶች በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ ሉዓላዊ መንግሥታትን መብትና ኃላፊነት ሊወስኑ አይችሉም።

አንዳንድ የግብፅ ወገኖች እነዚህ ስምምነቶች “ታሪካዊ መብት” እንደፈጠሩ ቢከራከሩም ኢትዮጵያ ይህንን ትርጓሜ አትቀበለውም።

እንደ ኢትዮጵያ ገለጻ፤ ያልተወከሉና ያልተማከሩ ሀገራትን ወክሎ የዓለም አቀፍ ወንዝ ውሃን ለመመደብ ማንኛውም የቅኝ ገዥ ኃይል ሥልጣን አልነበረውም።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዓባይ የጋራ ዓለም አቀፍ ወንዝ በመሆኑ አስተዳደሩ በዘመናዊ የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ መርሆች ሊመራ እንደሚገባ ትከራከራለች።

እነዚህ መርሆች ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም፣ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ትብብር እና ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ግዴታን ያጠናክራሉ። በዚህ መሠረት ማንኛውም ሀገር በዓባይ ላይ ብቸኛ ባለቤትነት ወይም ፍጹም መብት የለውም፤ የአንድ ሀገር የልማት ፍላጎትም የሌሎችን ሀገሮች የልማት መብት ለዘላለም ሊገድብ አይገባም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዋናነት የተገነባው ለከፍተኛ የመስኖ ልማት ሳይሆን ንጹህና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው። ኢትዮጵያም ፕሮጀክቱ የንጹህ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የሃገሪቱንና የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማጠናከር እንዲሁም በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብርን ለማሳደግ እንደተነደፈ በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥርና የልማት ፍላጎት እየጨመረ በመሆኑ ኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ አካታችና በትብብር የተመሠረተ የውሃ አስተዳደር ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን ታስረዳለች።

የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የተደራደሩበት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የዚህ አቀራረብ መገለጫ መሆኑንም ትገልጻለች። ስምምነቱ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀምን በማበረታታት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ትብብርንና ዘላቂ የሀብት አስተዳደርን ለማጠናከር ያለመ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን አጽድቀውታል።

ከኢትዮጵያ እይታ አንጻር በዓባይ ተፋሰስ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና የሚረጋገጠው አብዛኛዎቹን የተፋሰሱ ሀገሮች ካገለሉ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች በመነሳት ሳይሆን በመተማመን፣ በትክክለኛ ውይይት፣ በፍትሕ፣ በትብብር እና በዘመናዊ የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ መርሆች ላይ በመመስረት ነው።

ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ስምምነቶች ላይ ከመተማመን ይልቅ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅም እና በዘላቂ ልማት ላይ የተመሠረተ የወደፊት ትብብር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየሰራች ነው:: ይህም ለአሁኑም ሆነ ለሚመጡት ትውልዶች የሀገራትን መረጋጋትና ብልጽግና የሚያረጋግጥ ገንቢ መንገድ መሆኑን ታምናላች።

በብርሃኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review