AMN- ሐምሌ18/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተቀመጡት ስምንት አጀንዳዎች ላይ የሚደረገውን ውይይት በማጠናከር ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገሩን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መሥፍን አርዓያ ገለጹ።
ዋና ኮሚሽነሩ እንዳሉት ፣ በ10 አባላት ንዑስ ቡድኖች ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ውይይት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የተሰበሰቡት ሃሳቦች በሰብሳቢዎችና በጸሐፊዎች አማካኝነት ለ50 አባላት ቡድኖች መቅረብ ጀምረዋል።
ሃሳቦቹ ተጨማሪ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ለ250 አባላት ቡድኖች እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች በመከባበር፣ በመደማመጥና በነፃነት ሃሳባቸውን እያቀረቡ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር መሥፍን ፤ የተለያዩ ዕይታዎችን በአንድ የጋራ አቋም ለማቀናጀት የሚደረገው ሂደት ለጉባኤው የመጨረሻ ግብ የሆነውን መግባባት ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን ያለው የጉባኤው ሂደት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው ፣ ሀገራዊ ምክክሩ በውይይትና በመግባባት ለኢትዮጵያ ዘላቂና አዋጭ መፍትሔ ለማምጣት አስፈላጊ ሂደት መሆኑን ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ ተናግረዋል።
አጠቃላይ እስከ አሁን ያለው የጉባኤው ሂደት በአዎንታዊ መልኩ በተያዘው የአመራር ሥርዓት መሠረት እየቀጠለ መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።