አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ጋር ተወያዩ

You are currently viewing አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ጋር ተወያዩ

AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃንን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሳሂባጋፋሮቫ (ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸው ጋር በፓርላማ ትብብር፣ በኢኮኖሚ ግንኙነት፣ በቀጣናዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አቶ አገኘሁ ተሻገር የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው በማነጋገራቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ጉብኝቱ በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን ግንኙነት ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያንጸባርቅ አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በባኩ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በኢትዮጵያና በአዘርባጃን ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን በማስታወስ በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኃይል፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች የጋራ ትኩረት በሚሹ ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማሳደግ ጠንካራ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።

ከጥር 7 እስከ 8 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው 3ኛው የኢትዮ-አዘርባጃን የፖለቲካ ምክክር መድረክ የሁለቱን ሀገራት የፖለቲካ ትስስር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን ጠቅሰው የዕውቀትና የልምድ ልውውጡ በቀጣይም ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

በተለይም አዘርባጃን ለኢትዮጵያ የ”መሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማሻሻያ ያደረገችውን ድጋፍ በማድነቅ ትብብሩ በመንግሥት አገልግሎት ዘመናዊነት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እያካሄደች የምትገኘውን ሀገራዊ ሪፎርም በስፋት በማብራራት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሰላምና የብሔራዊ መግባባት ግንባታ ሂደትን ለማጠናከር ያለውን ሚና አብራርተዋል።

በተጨማሪም የአረንጓዴ ዐሻራና የኮሪዶር ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ጥበቃን፣ ዘላቂ ልማትንና የከተሞችን ዘመናዊነት ለማፋጠን የሚያገለግሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በፓርላማ ዲፕሎማሲ ዘርፍ፣ የሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ቡድኖች በሕግ አወጣጥ፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በዲጂታል ፓርላማ ሥርዓት፣ እንዲሁም የሕዝብ ተሳትፎን በማጎልበት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ እንደሚችሉ ገልጸው በተለይ የወጣቶችና የሴቶች የፓርላማ አባላት ትስስር መጠናከር የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደሚያሳድግ አንስተዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዘርፍም ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የተፈጠሩትን አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመጠቀም ከአዘርባጃን ጋር የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስሯን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰዋል።

በማዕድን፣ በዘይትና ጋዝ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቱሪዝም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች ያለው ትብብር ለሁለቱም ሀገራት ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝም መግለጻቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ የአዘርባጃን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በአገልግሎትና በቱሪዝም ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄዱ የንግድ ፎረሞች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት ላይ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጣለች ያሉት አፈ ጉባኤው ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋን በሰላማዊ መንገድና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሠረት ለመፍታት ያላትን አቋም አስረድተዋል።

በባለብዙ ወገን ትብብር ዙሪያ ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ሪፎርም፣ በዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ሂደት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች ትብብሯን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ ኢትዮጵያ የ2027 የCOP 32 የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ለማስተናገድ በምታደርገው ጥረት የአዘርባጃንን ድጋፍና አጋርነት ጠይቃለች።

ሁለቱ ሃገራት በፖለቲካ፣ በፓርላማ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በኃይል፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች የጋራ ትኩረት ባላቸው ዘርፎች ያለቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ለማሳደግና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review