ከታሪካዊ ወዳጅነት የጀመረው የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

AMN- ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከተለመደው የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ባለፈ፣ በተጨባጭ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢኮኖሚ አጋርነት እና በሰው ኃይል ልማት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂካዊ ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል።

የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ በ12ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታዋቂው የአዘርባጃን ገጣሚ ሙጂራዲን ቤይላቃኒ እናት፣ ኢትዮጵያዊት እንደነበረች የታሪክ ሰነዶች ይጠቁማሉ።

በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት የትምህርት ትስስር ከ1960ዎቹ ጀምሮ የቆየ ሲሆን፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአዘርባጃን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ሁለቱ ሀገራት መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 1992 የጀመሩ ሲሆን፣ አዘርባጃን እ.ኤ.አ. በ2015 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ በመክፈት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን አጠናክራዋለች።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ተጨባጭ የትብብር መስኮች የተሸጋገረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የመንግስት አገልግሎትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመን በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡

አዛርባጃን ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያተረፈችበት የ “አሳን ኪድሜት” የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ሞዴል ለኢትዮጵያ በማካፈል፣ በኢትዮጵያ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስተባባሪነት “መሶብ” የተሰኙ የህዝብ አገልግሎት ማዕከላት እንዲገነቡ አስችላለች።

ይኸው ትብብር ጎልብቶ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የአዘርባጃን ሪፐብሊክ የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ(ፕ/ር)፣ የመሶብ አገልግሎት ማዕከልን የጎበኙ ሲሆን፣ እንደ ሀገር በአንድ ዓመት የመሶብ አገልግሎት ጉዞ የተገኙ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አስመልክቶ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተከፈቱ የመሶብ ማዕከላት ከ150 በላይ የመንግስት እና የፌዴራል ተቋማት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በመስጠት የዜጎችን እንግልት እና ቢሮክራሲ የመቀነስ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

ከቴክኖሎጂ እና አገልግሎት ማዘመን በተጨማሪ፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ የአዘርባጃን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በማዕድን፣ በአቪዬሽን፣ በቱሪዝም እና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች እና የኢንቨስትመንት ተቋማት በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ በትምህርት እና በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ በሄይዳር አሊየቭ የትምህርት እድል እና የመንግስታዊ ስኮላርሺፖች አማካይነት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚሰጡ የነፃ የከፍተኛ ትምህርት እድሎች እየሰፉ መጥተዋል።

በተጨማሪም በአዘርባጃን ተምረው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማህበር በኢትዮጵያ ተቋቁሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እና የባህል ልውውጡን በማጠናከር ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ እና በባኩ መካከል ያለው ይህ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ትሥሥር፣ በታሪካዊ አጋርነት ላይ ተመስርቶ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የንግድ ትስስር እና የኢኮኖሚ እድገት የተሸጋገረ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ሆኖ ቀጥሏል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review