በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ እገዛ የሚያደርጉ የክልል ጉባዔ አባላት ምርጫ ተካሄደ

AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ እገዛ የሚያደርጉ የክልል፣ ከተማ አስተዳደር እና የፌዴራል ተወካዮችን ያካተተ ጉባዔ ምርጫ አካሂዷል፡፡

ከሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና ከፌዴራል መንግስት የመጡ ተወካዮች በውሳኔው ላይ ተገቢውን ተሳትፎ በማድረግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን አካላት ድምፆች እንዲሰማ ማድረግ የዚህ ጉባዔ አንዱ ዓላማ ነው፡፡

በሌላ በኩል በምክክር ቡድኖች የተዘጋጁ ምክረ-ሃሳቦች ወይም ውሳኔዎች ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ከማለፋቸው በፊት በሰፊው የክልል ተወካዮች ቡድን እንዲፀድቁ በማድረግ የምክረ-ሃሳቦችን ተቀባይነት ለማረጋገጥ ይረዳል ተብሏል፡፡

በጉባዔው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እያንዳንዳቸው 22 ተወካይ አባላት እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

በፌዴራል ደረጃ የሚወከሉ ባለድርሻ አካላት 22 ወኪሎች እንዲኖራቸው ተደርጎ፣ በአጠቃላይ 336 የጉባዔ አባላት በተመካካሪዎች መመረጣቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

እነዚህ ተወካይ የጉባዔ አባላት አካራካሪ እና ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች መቋጫ እንዲያገኙ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ሚና ይኖራቸዋል ያለው ኮሚሽኑ፤ ነገር ግን ሁሉም ርዕሰ ጉዳይ ወደ ጉባዔ ለውሳኔ አይቀርብም ብሏል፡፡

ርዕሰ ጉዳዮች ለውሳኔ እንዲቀርቡ የሚደረገው በሥራ ቡድን ደረጃ የተወሰነ ውሳኔ ቢያንስ 3 ክልሎች ጉዳዩ በክልል ተወካዮች ጉባዔ እንዲታይና እንዲወሰን ግልፅ የሆነ ጥያቄ ለኮሚሽኑ ሲያቀርቡ፤ ከአስማሚ ግብረ-ኃይል ጥረት በኋላ በሥራ ቡድን ደረጃ የሚፈለገው ድምፅ ባለመገኘቱ ምክንያት ውድቅ የተደረገ ጉዳይ ሲኖር እና ጉዳዮ የሕዝቦችን እሴት፣ ማንነት እና ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ ሲታመንበት እንደሆነ ኮሚሽኑ ባስቀመጠው የውሳኔ አሰጣጥ መመሪያ ላይ ተመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ የጉባዔ አባላት ምርጫ ያካሄደው ከሐምሌ 22/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲመክሩ የነበሩት 16 ባለ 250 አባላት ስልታዊ ቡድኖች ሃሳባቸውን በቃለ ጉባዔ የጋራ በማድረግ በቀጣይ ለሚደረገው የ500 ተመካካሪዎች ቡድን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review