AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ካለችበት የታፈነ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራት ወጥታ ወደ ተደመረ ብልፅግና እንድትሸጋገር ታላላቅ ጥረቶች መደረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በለውጡ ማግስት ከአማራ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከውይይቶቹ ጀርባ የነበሩ ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።
በዚህም ለውጡ እንደመጣ ከመጀመሪያዎቹ ተግባራት አንዱ ወደ ሕዝብ ወርዶ ጥያቄዎችን፣ አስተያየቶችንና ፍላጎቶችን ማዳመጥ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጎንደር ላይ የወጣቶች “የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” የሚለው መፈክር ብቻ ሳይሆን የታሪክና የደም ውህደት መግለጫ የነበረውን እውነት በመያዝ ሕዝቦችን የማቀራረብ ሥራም ተሰርቷል ብለዋል።
ለዚህም የቻይናን ተሞክሮ በማሳያነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቻይና የዴንግ ዚያኦፒንግ ዘመን ኢኮኖሚው ብቻ ተከፍቶ ፖለቲካው በመታፈኑ የተፈጠረውን የደም መፋሰስና ቀውስ አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ፖለቲካውንም ሆነ ኢኮኖሚውን ጎን ለጎን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ታምኖበት መሰራቱን ነው የተናገሩት።
ውህደትና ትብብር ያለ ጥልቅ የእምነትና የሐሳብ መግባባት ከተደረገ ፈራሽነቱ ፈጣን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ያማከለ “መደመር” የተሰኘው ሀገራዊ ፍልስፍና ተቀርጾ ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ መጀመሩን ተናግረዋል።
በታምራት ቢሻው