AMN – ነሐሴ 8 /2018 ዓ.ም
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ፈጣን ምላሽ ሰጪና አስቀድሞ ስጋቶችን መከላከል የሚችል ስትራቴጂካዊ መቺ ኃይል ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ አድርጋ ገና ሳትረጋጋ በባንዳዎች በተፈተነችበት ወቅት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሠራዊት የተደቀነውን አደጋ በመቀልበስ ረገድ ከባድ የተጋድሎ ትግል አድርገዋል ብለዋል።
ዕዙ የኢትዮጵያ ጠንካራ ክንድ የህዝቦቿ መተማመኛ ልዩ ኃይል መሆኑን በማብራራት እስከ አሁን ለሀገር ለከፈለው ዋጋ ኢትዮጵያ እንደምታከብረውና ነገም ይህንኑ ልዩ ብቃቱን ይዞ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
ሠራዊቱ የውጭ ጠላት ከመከላከል ባለፈ፣ የአገር ውስጥ ሰላምን በማጽናት ሀገራዊ ህልውናችን ተጠብቆ ዕድገት እንዲቀጥል የሚያስችል፣ የሀገር አንድነትና የህግ የበላይነት እንዲከበር የዜጎች ክብር መገለጫ ነው ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
ባንዳ ለሆዱ ሲሞት እኛ ለሀገር ሉዓላዊነት ለህዝቦች ክብርና አንድነት እንሞታለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሻዕቢያ ከጅምሩ ኢትዮጵያን ከባህር በር ለማራቅ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ጥምረት ፈጥሮ ኢትዮጵያ ላይ ደባ የሰራ ኃይል ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ህወሃትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሸጠና ለ27 አመታት ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ጠንክሮ የሰራ ቅጥረኛ የገዛ ሀገሩን ሠራዊት ያጠቃ የክህደት ኃይል ነው ሲሉ ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሕወሃት ክህደት የተፈተነች ነገር ግን ፀንታ የቆመች የልዩ ዘመቻ ሠራዊት መሰል ጠንካራ አርበኛ ልጆች ያሏት ሀገር ስለሆነች ጉዞዋን ቀጥላለች ብለዋል።
ፅንፈኞቹን ፋኖንና ሸኔን ጨምሮ አራቱም የጥፋት ኃይሎች በባዕዳን ስትራቴጂ ሥር ተሰልፈው ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ ፅምዶ የተባለ ጥምረት ቀርፀው ሕዝባችንን ለስቃይና መከራ በመዳረግ ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ጓጉተው ቢሠሩም ይህ ፍላጎታቸው መቼም ሊሳካ እንደማይችል አሳይተናቸዋል ብለዋል።
ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በመከፋፈል እርስ በእርሱ እንዳይተማመን ያደርግ እንደነበረ አውስተው የትግራይን ህዝብ ደግሞ የኢትዮጵያ ልጆች እየመጡብህና እየከበቡህ ነው እያለ ከወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ ሲሰራ የኖረ እኩይ ፖለቲካ አራማጅ ፀረ ሀገር ኃይል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዛሬ ያ ሁሉ ሴራ ከሽፎ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን መሰሪ ቡድን መጥፎ ተግባር በመረዳቱ ወያኔ ከህዝብ ተነጥሎ መንጠልጠያ ሲያጣ የቀድሞ ጠላቶቹን ሸኔንና ፅንፈኛ ፋኖን አቅፎ ሻዕቢያን ዳግም አዝሎ የትናንት ክህደቱን በአደባባይ እየደገመው ይገኛል ብለዋል፡፡
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በአሁኑ ወቅት በትጥቅም በሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በማስታወስ ለሰፈር ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አቅጣጫ በሀገር ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንዳለበት ማሳሰባቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል።