የዓለም አቀፉ የኅብረት ሥራ ጥምረት በመጪው ጥቅምት ወር ኮንፈረንሱን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ማቀዱን አስታወቀ

AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የዓለም አቀፉ የኅብረት ሥራ ጥምረት በመጪው ጥቅምት ወር ኮንፈረንሱን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ማቀዱን አስታውቋል።

የዓለም የኅብረት ሥራ ጥምረት በአፍሪካ (ICA-Africa) ዳይሬክተር ሮዝ ካሪሚ (ዶ/ር) ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂደዋል።

ጥምረቱ በመጪው ጥቅምት ወር በርካታ ሀገራት የሚሳተፉበትን እና በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የኅብረት ሥራ ኮንፈረንስ ዝግጅት አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አመራሮች ጋር መክሯል፡፡

በዚሁ ወቅት ዋና ዳይሬክተሯ ሮዝ ካሪሚ (ዶ/ር)፤ ከአዲስ አበባ የህብረት ስራ ኮሚሽን አመራሮች ጋር በመሆንም በመዲናዋ ማኅበራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

አዲስ አበባ ላይ የጎበኟቸው የህብረት ስራ ማህበራት ተሞክሮ የሚቀሰምባቸውና አርኣያነት ያላቸው መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ቀጣዩን ዓለም አቀፍ የህብረት ሥራ ጉባዔ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ውሳኔ መተላለፉም የዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀብተየስ ዲሮ በበኩላቸው፤ የመዲናዋ ህብረት ሥራ ማህበራት የተቋቋሙበትን አላማ ከማሳካት አንፃር አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልፀው ዓለም አቀፍ የኅብረት ሥራ ጥምረት በአፍሪካ ጉባዔ በአዲስ አበባ ሲካሄድም ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን ለመቅሰምና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review