AMN- ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በምንም መለኪያ የአማራን ህዝብ የሚጎዳ ሳይሆን የሚጠቅም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት የአማራ ክልልን ጥቅም ያሳጣል ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ስምምነቱ ለትግራይ፣ ለአማራ፣ ለአፋር እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም በማምጣት ወደ ልማት እንድናተኩር አድርጓል ብለዋል።
በክልሉ እየተሰሩ ያሉ በርካታ የልማት ስራዎችም ከስምምነቱ በኋላ የተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ስምምነቱ ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አካባቢዎች ጥቅም ያስገኘ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህን የተሳሳቱ ሀሳቦች የሚያራምዱ አካላት ስምምነቱን በበቂ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማንኛውም ሰው ስምምነቱን አንብቦ ሊረዳው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ስምምነቱ በውስጡ ዋና ዋና አንኳር ጉዳዮች እንዳሉት ያብራሩ ሲሆን፣ በዋነኝነት በአንድ ሀገር ሁለት መከላከያ አያስፈልግም በሚል የታጠቁ የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ እና በኢትዮጵያ አንድ የታጠቀ ኃይል ብቻ እንዲኖር ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው በትግራይ የተካሄደው ህገ-መንግስታዊ ያልሆነ ምርጫ ቀርቶ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ማድረግ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
ይህም የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በመሆኑ አማራን በምንም መልኩ የማይጎዳ መሆኑን ነው የገለጹት።
ህገ-መንግስቱ እንዲከበር እና የክልል መንግስታት ከስልጣናቸው ውጭ ከሌሎች ሀገራት መንግስታት ጋር በመሆን የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲያቆሙ ማድረግም ዋና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም የፈረሱና የተጎዱ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ መገንባት እና አገልግሎቶችን ማስጀመር የሰላም ስምምነቱ አንኳር ጉዳዮች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በትዝታ መንግስቱ