AMN ሐምሌ 27/2018
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ እንድታጌጥና የአፈር ለምነቷ እንዲመለስ ማስቻሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በየካ ተራራ በመገኘት በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተሳትፏቸውን አሳድጓል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን በመግለጽ፤ ይህም የኢትዮጵያ የአፈር ሀብት ከመሸርሸር ታድጓል ብለዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ እንድታጌጥና የአፈር ሀብታችንን ከመሸርሸር መታደግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በበርካታ አካባቢዎች ጠፍተው የነበሩ ምንጮችና ሀይቆች እንደገና እንዲያንሰራሩና እንዲመለሱ አስችሏል ብለዋል፡፡
ዛሬ የሚተከሉ ችግኞች ከዚህ ትውልድ የተሻገሩ የመጭው ትውልድ ተስፋዎች ጭምር ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኮፕ (COP 32) ጉባኤን እንድታዘጋጅ የተመረጠችበት አንዱ ምክንያት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያስመዘገበችው ድንቅ ውጤትና ያገኘችው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እውቅና መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጉባኤው ከስብሰባነቱ ባሻገር የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ስኬት በአካል የሚያይበትና ልምድ የሚቀስምበት ታላቅ መድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡