ኢትዮጵያ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በአዲስ መልኩ እየቀረጸች ነው-ፈርስት ፖስት

You are currently viewing ኢትዮጵያ የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በአዲስ መልኩ እየቀረጸች ነው-ፈርስት ፖስት

AMN – ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም

ታዋቂው የሕንድ የዜና ሚዲያ ፈርስት ፖስት ባወጣው የዘጠኝ ደቂቃ ዘገባ ፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሽግግርና በቀጣናው እያሳደረች ያለችውን ተጽዕኖ በስፋት ዳሷል።

እንደ ፈርስት ፖስት ዘገባ፣ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛና የጥንታዊ መንግስታት ምድር ከመሆኗ ባሻገር፣ አሁን ላይ ከቀድሞ ገናና ታሪኳ ጋር የሚመጥን አዲስ ጉዞ ላይ ትገኛለች።

ዘገባው ቀደም ሲል ሀገሪቱ በጦርነት፣ በድርቅና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ትታወቅ እንደነበር አስታውሶ ፤ ዛሬ ግን በኢነርጂ፣ በአቪዬሽን፣ በማዕድንና በዲጂታል ኢኮኖሚ እያከናወነቻቸው ባሉ አስደማሚ ስራዎች ያንን የተዛባ ትርክት በጽኑ እየቀየረችው መሆኗን ገልጿል።

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የኢነርጂ አብዮት

በሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ከ5 ሺህ ሜጋዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጎላ ድርሻ እንዳለው የተቀመጠ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ከኮንክሪትና ከተርባይን በላይ ለኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ነፃነትና እራስን የመቻል ትልቅ ሐውልት መሆኑን ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ምርቷን ለኬንያ፣ ለጂቡቲ እና ለሱዳን በመሸጥ ኤሌክትሪክን ወደ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛነት ከመቀየሯም በላይ የምስራቅ አፍሪካ የትስስር ማዕከል መሆን መቻሏን አብራርቷል።

የአቪዬሽን እና የመሠረተ ልማት መፋጠን

በአቪዬሽን ዘርፍ፣ አህጉራዊ ግዙፍነቱን ያስጠበቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላቀ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት መሸጋገሩን ዘገባው ጠቅሷል።

በተለይም በ12.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት እስከ 110 ሚሊዮን ተጓዦችንና 4 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም የሚኖረው በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባንና አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ጋር የሚያገናኝ ዋና የመተላለፊያና የዲፕሎማሲ መናኸሪያ ያደርጋታል ብሏል።

ግብርና፣ ማዕድን እና ዲጂታላይዜሽን

ዘገባው እንደገለጸው፣ ሀገሪቱ ከግብርና ጥገኝነት በመውጣት የወርቅ ምርትን ከዋና ዋና የወጪ ንግዶቿ አንዱ ማድረግ ችላለች።

በግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት በሶማሌ ክልል የሚገነባውና በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን ዩሪያ የሚያመርተው የማዳበሪያ ፋብሪካ የውጭ ጥገኝነትን እንደሚቀንስ አመላክቷል።

በተጨማሪም የ“5 ሚሊዮን ኮደርስ” ኢኒሼቲቭ ፣ የ4G/5G ቴክኖሎጂ መስፋፋት እንዲሁም እንደ ቴሌኮም፣ ባንክና የካፒታል ገበያ ያሉ ዘርፎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸው ኢኮኖሚው ከመንግስት ቁጥጥር ወደ ግል ዘርፍ መሪነት እየተሸጋገረ መሆኑን ማሳያ ናቸው ብሏል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗንና ከቻይና፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከምዕራባውያንና ከቀረው አፍሪካ ጋር ያላትን ሁለገብ ትብብር በማጠናከር ጎራ ሳትለይ እየሰራች መሆኗን የጠቆመው ፈርስት ፖስት ፤ ይህ ሁለገብ የኢኮኖሚ ሽግግር በቀጣዮቹ ዓመታት የመላውን አህጉር ገጽታ በአዲስ መልኩ የሚቀይር እንደሆነ አመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review