AMN-ሰኔ 8/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላፉት መልእክት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ብሔራዊ ሥራችን ከተፈጥሮ የመታረቅ፣ በልማት የመላቅ አዲስ ጎዳና ነው ብለዋል፡፡

ለአንዲት ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሕዝብ ተደምረን በሠራነው የአረንጓዴ ዐሻራችን፣ ልምላሜ የተራቡ ተራሮች አረንጓዴ ለብሰዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምንጮች እና ተፋሰሶች ምድሩን አረስርሰዋል ብለዋል።

በረሃማነት ይጸናባቸው የነበሩ ክበበ ምድሮች ነፋሻማ ሆነዋል። የተፈጥሮን ጫና ተቋቁመናል! ይህ ደግ የተፈጥሮ ዕርቅ ነው።
የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥን ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር በማስተሣሠር በተሠራው ሥራ የፍራፍሬ ተክሎች በስፋት ለምተዋል፤ ፍሬ መስጠትም ጀምረዋል ሲሉም ገልጸዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ።
ይህም በምግብ ራስን ለመቻል ለጀመርነው ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ተደማሪ ዐቅም ሆኗል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ ልጆች ከፖለቲካ አሰላለፍ አልፈው፣ ከሐሳብ ተቃርኖ ተሻግረው፣ ገጸ ብዙ ልዩነቶችን አሸንፈው ለሀገርና ለትውልድ አስበው ያሳኩት የመተባበር ድል፣ የተጨበጠ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ስንተባበር ትርፋችን እልፍ፣ ዕቅዳችንም የተሳካ የሠመረ ይሆናል።
የዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ የእስከ ዛሬ ድካማችን መደምደሚያ፣ የድላችን መዳረሻ፣ በድል ላይ ቆመን ለሌላ የላቀ ድል የምንነሣበት ልዩ ዓመት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሁላችንም በሩጫ ትግል ሊያልቅ ሲል እንደሚበረቱት ሊጠናቀቅ ሲል እንደሚፈጥኑት ጀግኖች አትሌቶቻችን ካለፉት ዓመታት አስበልጠን እንትከል! እንበርታ!እንፍጠን! በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡