በመዲናዋ እየተተገበረ ያለው የዲጂታል አሰራር ከተማዋን በማዘመን የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን እያቀላጠፈ ነው

You are currently viewing በመዲናዋ እየተተገበረ ያለው የዲጂታል አሰራር ከተማዋን በማዘመን የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን እያቀላጠፈ ነው

AMN – ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ እና የስማርት ወይም ስሉጥ ከተሜነት ጉዞዋን የሚያፋጥኑ ዘመናዊ የዲጂታል አሰራሮች በስፋት እየተተገበሩ ይገኛል፡፡

በከተማዋ የህዝቡ የረጂም ጊዜ ጥያቄ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማስተካከል መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና የሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከታየው የከተሜነት ዕድገት ጎን ለጎን የነዋሪውን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ዘመን ተሸጋሪ ሰው ተኮር ስራዎችም ተከናውነዋል፡፡

እነዚህም በከተማዋ የተከናወኑና ተግባራዊ የተደረጉ ሥራዎች ከተማዋን በማዘመን የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን እያቀላጠፉ ሲሆን የነዋሪዎችን የእለት ተእለት ኑሮ በማሻሻል ረገድም ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን አስገኝተዋል፡፡

በዋና ዋና መንገዶች የተገጠሙ የሲሲቲቪ ካሜራዎች ወንጀልን ለመከላከል፣ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንዲሁም የትራፊክ ፍሰትን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ስሉጥ ከተሜነት የከተሞችን አገልግሎት እና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የመረጃ ቴክኖሎጂን በስፋት በመጠቀም አገልግሎትን ዲጂታል ማድረግን ያካትታል፡፡

በዚህም ወረቀት አልባ የህክምና አገልግሎት፣ የዲጂታል መታወቂያ አሰጣጥ፣ የማስታወቂያ ቦርዶች ዲጂታላይዜሽን፣ የትራፊክ አስተዳደር፣ የተቋማት መረጃ ትስስር ተግባራዊ ከተደረጉ የመዲናዋ ዋና ዋና የዲጂታል አሰራሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የስማርት ወይም ስሉጥ ከተማ ዓላማ የተቀናጀ፣ ፈጣን፣ አካታችና ቀልጣፋ የመንግስት አሠራር በመዘርጋት ጥራት ያለው የአገልግሎት ስርዓት መፍጠር ነው።

ከዚህ በፊት የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ነዋሪዎችን ለእንግልት የሚዳርግ፣ ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍት፣ ግልፅነት የሌለው እንዲሁም የከተማዋን እድገትም ጭምር የሚፈታተን አሰራር እንደነበር ይነገራል፡፡

ስማርት ወይም ስሉጥ ከተማ ፍጥነት፣ ቅልጥፍና፣ ጥራትና ግልፀኝነት ያለው አገልግሎት በመስጠት የከተማዋ ነዋሪዎች በመንግስት ላይ ያላቸውን እምነት እንዲጨምርም ያደርጋል፡፡

ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ዲጂታል አሰራርን በመተግበር ሂደት ውስጥ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡

ክፍለ ከተሞች ከወረቀት አሰራር እንዲሁም ተገልጋዮችን ለእንግልት ከሚዳርግ ሂደት ወጥተው ወደ ወረቀት አልባ ዘመናዊ የዲጂታል አሰራር ተሸጋግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስማርት ሲቲ ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ ወረቀት ላይ የተመሰረቱ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ማሸጋገሯ ነዋሪዎች ያለ እንግልት በፍጥነት ባሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review