ሕዝቡ የጸረ-ሙስና ትግሉ ባለቤት እየሆነ መጥቷል

AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

በሀገሪቱ ግንዛቤ ለመፍጠር በተሰሩ ስራዎች ሕዝቡ የጸረ-ሙስና ትግሉ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ኮሚሽኑ ያሰናዳው በ17ኛው ሀገር አቀፍ የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ትስስር ጉባኤ ተካሂዷል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በፀረ-ሙስና እና ስነ-ምግባር ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ዋነኛውና ትልቁ ማእቀፍ የሆነው የትውልድ ሥርዓት ግንባታ ጥሩ አቅጣጫ ይዟል።

በዚህ ረገድ በፀረ-ሙስና ትግል ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኘው ሕዝብ ግንዛቤን ለማስረፅ በተሰራው ስራ ሕዝቡ የሙስና ትግሉ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ሕዝቡ ሙስና በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የሰላም አለመረጋጋትን ከሚፈጥሩ ችግሮች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ተግዳሮት መሆኑን በጽኑ አቋም በማመን መንግሥት ችግሩን እንዲገታ ያለውን አቋም በተለያዩ መድረኮች ማሳወቁ ለፀረ ሙስና ትግሉ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

አሁን ላይ መንግሥት በሙስና ላይ የያዘው አቋምና እርምጃ ችግሩን ለማስወገድ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ትግሉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ጊዜው የሚጠይቀውን የአሰራር፣ የትብብርና የቅንጅት ስራን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ ባለፈው በጀት ዓመት የፀረ-ሙስና ትግሉ በሥነ-ምግባር ግንባታ፣ ሙስናን አስቀድሞ መከላከልና ሕግ ማስከበር እንዲሁም የአንድ ዕቅድ የአንድ ሪፖርት ስትራቴጂዎች በመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ አፈጻጸም ማከናወኑን አብራርተዋል።

የክልልና የከተማ አስተዳደር የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ቀደም ሲል 16 ዙር ሀገር አቀፍ የትስስር ጉባኤዎች መካሄዳቸው ለጸረ-ሙስና ትግሉ ፍሬያማ እንዲሆን ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

17ኛው ጉባዔም በ2018 በጀት ዓመት ሲከናወኑ በነበሩ የሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ስራዎች በጥልቀት በመወያየት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review