AMN – መስከረም 20/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቀጣዩ የአስተዳደሩ የሥራ አፈጻጸም ዋነኛ መለኪያ የፕሮጀክቶች ብዛት ወይም የቁጥር ሪፖርት ሳይሆን የነዋሪዎች እለት ተእለት ኑሮ ላይ የሚመጣ ተጨባጭ መሻሻል እንደሚሆን ገለጹ።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤን በድጋሜ የከተማ ከንቲባ አድርጎ ሰይሟል፡፡
ከንቲባዋ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግግር ፣ ከእንግዲህ ልማታችንን የምንለካው በሰራነው ፕሮጀክት ብዛት ሳይሆን የአንዲት እናት የኑሮ ጫና ምን ያህል ቀነሰ፣ ወጣቶች ምን አይነት ጥራት ያለው የስራ እድል አገኙ፣ ነጋዴዎች ያለ እንግልት አገልግሎት አገኙ ወይ፣ እንዲሁም ቤተሰቦች ምን ያህል የተሻለ ትምህርት፣ ጤና፣ ውሃና ትራንስፖርት አገኙ በሚለው ይሆናል ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት የከተማዋን ገፅታ ለመቀየርና መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት የተሰሩ ስራዎች የተሳኩ መሆናቸውን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች ፣ በቀጣይ ግን ትኩረታቸው ቀጥታ በዜጎች ህይወትና አኗኗር ላይ አዎንታዊ ለውጥ በሚያመጡ ዘርፎች ላይ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ከንቲባዋ ዜጋን በክብር የሚያገለግልና ከሙስና የፀዳ ተቋም የመገንባት አስፈላጊነትን ያነሱ ሲሆን፣ በአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ መሰረት በብቃት ላይ የተመሰረተ፣ ፈጣን እና ዘመናዊ አገልግሎት እንደሚስፋፋ ተናግረዋል።
ሙስናንና ሌብነትን የማይታገስ አሰራርና ስርዓት በመዘርጋት የመንግስት አገልግሎት በገንዘብና በጉቦ የሚሸጥ ሳይሆን የዜጋው መብት እንዲሆን እንደሚሰራና አዲስ አበባን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይ ዋነኛ ማዕከል ለማድረግ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች በተፋጠነ ሁኔታ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ዘመናዊ የገበያ ስርዓትን ለማስፋፋት በትጋት እንደሚሰራ የጠቆሙት ከንቲባዋ ፣ ለወጣቶች ፣ ለሴቶችና ለከተማዋ ነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድል ማመቻቸት የቁልፍ ትኩረት መስክ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢንቨስትመንትን፣ አነስተኛና መካከለኛ እንዱስትሪዎችን፣ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችንና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በመደገፍ ከተማዋ ሀብትና እድል የሚፈጠርባት እንድትሆን በቀን 24 ሰአት ሳምንቱ ሙሉ እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል።
አዲስ አበባ ለኑሮ የምትመችና የነዋሪዎችን ክብር የምትጠብቅ ከተማን ማስቀጠል ዋና ትኩረት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ ጥራት ያለው ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታን በማስፋፋት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃ፣ የመንገድና የትራንስፖርት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የከተማዋን እድገት ለማረጋገጥ አመራሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነዋሪ ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነትና ባለቤትነት በመሸጋገር በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በታደሰ ሽፈራው