AMN- መስከረም 20/2019 ዓ.ም
ያለፉትን አምስት ዓመታት “የከተማችንን መልክ እንቀይራለን፤ የሕዝባችንን ክብር እንመልሳለን፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ እናስመስላታለን” ብለን የገባነውን ቃል ከጠበቅነው በላይ ተሳክቷል፡፡
ሆኖም የትናንቱ ስኬት የነገውን ኃላፊነት አይተካም። ትናንት የከተማችንን ገጽታ ለመቀየር ሠርተናል፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ስራዎችን አከናውነናል። በቀጣዩ ምዕራፍ ደግሞ የነዋሪዎቻችንን የዕለት ተዕለት ኑሮ በተጨባጭ ማሻሻል የሚችሉ ስራዎች የምናከናውንበት ይሆናል። ከእንግዲህ ልማታችንን የምንለካው በሠራነው ፕሮጀክት ብዛት እና በቁጥር በሚተነተን ሪፖርት ብቻም አይሆንም። ይልቁንም አንዲት እናት ምን ያህል የኑሮ ጫና ቀነሰላት ? አንድ ወጣት ምን አይነት ኑሮውን የሚያሻሻልበት ሥራና ዕድል አገኘ?
አንድ ነጋዴ የመንግስት አገልግሎት ሳይንገላታ በክብር ማግኘት ቻለ ወይ?
አንድ ቤተሰብ ምን ያህል የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ ጥራት ያለው ት/ቤትና የጤና አገልግሎት ፣ ውሃ፣ መንገድና ትራንስፖርት አገኘ? የሥራችን የመጨረሻ ውጤት የእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ መለኪያ መሆን አለበት።

አዲስ አበባንችን ለኑሮ የምትመች፣ የነዋሪዎቿን ክብር የምትጠብቅ ከተማ ጥራት ያለው ሰፊ መሠረተ ልማት እንገነባለን። ያረጁና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን አድሰን፥ የንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድና የፍሳሽ መሠረተ ልማት፣ ትራንስፖርትና መኖሪያ ቤት ተደራሽነትን እናሻሽላለን።
ዘመናዊ የሕክምና ማዕከላትን በማስፋፋት፣ የግሉን ዘርፍ በማበረታታት፣ የጤና ቱሪዝምን በማሳደግ፣ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን በማጠናከርና የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነትና ጥራትን በማሻሻል ለኑሮ ተመራጭ የሆነች ከተማን እንገነባለን፡፡
በአጠቃላይ የምንፈልጋት አዲስ አበባ ሕፃናት በደህንነትና በተስፋ ቦርቀዉ የሚያድጉባት፣ ወጣቶች ጥራት ያለው ሥራና ዕድል የሚያገኙባት፣ ሴቶች መብታቸውን በእኩልነት የሚጠቀሙባት፣ ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች ምቹ የስራ ሁኔታ የሚያገኙባት፣ ሁሉም ነዋሪ ከተማዋን “የእኔ” ብሎ የሚኮራባት እና የሚገነባት ከተማ እንድትሆን ማድረግ ነው ።
አዲስ አበባ የሁላችን ቤት ናት። በመንግስት ብቻ የምትገነባ አይደለችም። የሁላችን ኃላፊነት ናት። የሁላችን ተስፋም ናት።
ትናንት ያየነው ለውጥ መዳረሻችን አይደለም፤ የቀጣዩ ጉዞ መነሻችን እንጂ። ከተባበርን እንችላለን፤ ከተጋን እናደርጋለን፤ አቅማችንን ካስተባበርን የበለጠ ውጤት ማምጣት እንችላለን።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተማችን የተመዘገቡ ስኬቶች የመላው ከተማችን ነዋሪዎች ፥ የንግድ ማህበረስብ ፥ የልማት አጋዥ የሆኑ ባለሃብቶች፥ ምሁራን የከተማ አስተዳደራችን አመራሮች፥ ሰራተኞች ፥ አጋር አካላት ፥ ሴቶች፥ ወጣቶች፥ የነቃ ተሳትፎ ድምር ውጤት በመሆኑ ከልብ እናመሰግናለን።
በቀጣይም የከተማችን ዕጣ ፈንታ በአመራሩ ትከሻ ላይ ብቻ የሚወድቅ አይደለምና የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ አብረን ፥ተደጋግፈን ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነትና ባለቤትነት በመሸጋገር፣ የጋራ ራዕይ ሰንቀን በጋራ እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ ።