ኮሚሽኑ በመዲናዋ የቱሪዝም መዳረሻዎችንና አገልግሎቶችን እያስፋፋ ነው

AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን የቱሪዝም መዳረሻዎችንና አገልግሎቶችን እያስፋፋ መሆኑን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የከተማዋን የቱሪዝም ዕድገት ለማፋጠን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አብራርተዋል፡፡

በዚህም የተቋሙን መዋቅራዊ አሰራር ማበጀት፣ የሰው ሃይል ማደራጀት፣ የቱሪዝም ልማት፣ የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የመደገፍና የመቆጣጠር ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በተለይም ከዚህ በፊት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ብቻ ይገኝ የነበረውን የቱሪስት መረጃ ማዕከል አገልግሎት ለማስፋት ታስቦ፣ በየካ ክፍለ ከተማ በሀገር ውስጥ የመጀመሪያ የሆነና ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር ምሳሌ ሊሆን የሚችል ዘመናዊ የቱሪስት መረጃ ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት መቃረቡን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በቀጣይም በኮሪደር ልማቱ ለለሙ እና ለዚህ ምቹ በሆኑ አምስት ተጨማሪ አካባቢዎች ማዕከላቱን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማጎልበትና የጉብኝት ባህልን ለማዳበር የሚያስችል የቱሪዝም ማበረታቻ ደንብ ረቂቅ መዘጋጀቱንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ወደ ከተማዋ በመጋበዝ ሰፊ የገጽታ ግንባታ ሥራ መከናወኑን የገለጹት ኮሚሽነር ሁንዴ፣ ይህም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ዘንድ ከተማዋን ለማስተዋወቅ ያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የቱሪስቶችን ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ጥራትን ለመጠበቅ እና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ማዕቀፎች እና የQR ኮድ የቅሬታ መቀበያ መድረኮችን በመዘርጋት ላይ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

ኮሚሽነሩ አያይዘውም በንግድ አዋጅ ማሻሻያዎች ምክንያት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የሚጠየቁባቸው ዘርፎች መቀነሳቸው ጠቅሰው ጥራቱን የጠበቀና ብቁ አገልግሎት ለከተማዋ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review