AMN — መስከረም 23/2019 ዓ.ም
ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን እንደ ትናንትናው የትግራይን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ ብሎ ምሎ የሚገዘትበት እና ሕዝቡን የሚያታልልበት ሥነ ልቦናም ሆነ ፖለቲካዊ አላማ የለውም።
ምክንያቱ ደግሞ ቡድኑ ከአባቱ ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ከማድረግ ጀምሮ ሃገሪቱን በተለያዩ መንገዶች ለማፍረስ ሲያሴር መቆየቱ ነው።
ቡድኑ ኢትዮጵያን የባህር በር ማሳጣት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የባህር ኃይል የበተነ፣ ሃገሪቱ በዘመናት ሂደት የገነባችውን ሃገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት ያዳከመና ሉዓላዊነቷን እንደ ሻዕቢያና ግብጽ አሳልፎ ለመሰጠት የሞከረ ነው።
ህገ ወጥ ቡድኑ ህገ መንግስታዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድና ሃገሪቱን መንግስት አልባ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጦርነቶችን ቢያካሂድም እኩይ አላማው ሊሳካለት አልቻለም።
ራሱ በለኮሰው እሳት ተቃጥሎ የፕሪቶሪያውን የሠላም ስምምነት ከፈረመ በኋላም ቢሆን የክልሉን ጊዜያዊ መስተዳድር በማንአለብኝነት አፍርሶ፣ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዳይረጋገጥ እንቅፋት እስከ መሆን ደርሷል።
ህወሃት ለትግራይ ሕዝብ ሰላምና ልማት የሚያስብና የሚጨነቅ ቢሆን ኖሮ የስልጣን ጥሙንና የገንዘብ ጥቅሙን ወደ ጎን ተቶ ለፈረመው ስምምነት ይገዛ ነበር ይላሉ የክልሉ ምሁራን። የሰሜኑ ጦርነት ከመከሰቱ በፊትም ሆነ በጦርነቱ ከተሸነፈ በኋላ፣ ጸብ አጫሪነቱን እንዲያቆም፣ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅምና የትግራይን ሕዝብ ሰላምና ልማት እንዲያስቀድም በተደጋጋሚ የተጠየቀው ቡድኑ ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።
መንግስት ያቀረበለትን የሰላም አማራጮች እንዲጠቀም በሃገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በፖለቲካኞች፣ በምሁራንና በታዋቂ ሰዎች ጭምር በተደጋጋሚ የተጠየቀው ቡድኑ፣ ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጓል።
ህገ ወጥ ቡድኑ የሚከተለው መንገድ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው፣ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማት የማያመጣ፣ ፍጻሜውም ጥፋት እንደሆነ በአፍሪካ መሪዎች ጭምር በተደጋጋሚ የተመከረ ቢሆንም የቀረቡለትን የሰላም አማራጮች መቀበል አልቻለም።
ቡድኑ ይልቁንም ራሱን ከኢትዮጵያ ሕዝብ በመነጠል እና ከሻዕቢያ፣ ጽምዶና ግብጽ ጋር ጥምረት በመፍጠር ኢትዮጵያን የማፍረስ አቋምና ፍላጎት እንዳለው በይፋ አረጋግጧል።
የህገ ወጥ ቡድኑ ዋንኛ አላማ የትግራይን ሕዝብ ነጻ ማውጣት ሳይሆን በሕዝብ ስም የሻዕቢያንና የግብጽን ተልእኮ ማሳካት መሆኑን ቀደም ብለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ የነበሩት የክልሉ ተወላጆች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት አባቶች አሁን ላይ መንግስት የህግ የበላይነትን እና የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እንዲያስከብር በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
በወንድማገኝ አሰፋ