AMN- መስከረም 23/2019 ዓ.ም
የዓባይ ውሃ አጠቃቀምና ፍትሃዊ ክፍፍል ጉዳይ ግብፅ በምታራምደው ግትር አቋም የተነሳ የአፍሪካ ቀንድና የሰሜን አፍሪካ ቀጣና የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አጀንዳ እንደሆነ ዘልቋል።
ግብፅ ማንንም ሳታማክር እጅግ ግዙፍና ውሃ አባካኝ የሆነ ግድብ ገንብታ ሌሎች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት ለማደናቀፍ ግን የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ይህን የግብፅን እኩይ አካሄድና የአስዋን ግድብ ጥፋትን የሚያጋልጥ ጽሑፍ አስፍረዋል።
የግብፅ አስዋን ግድብ በአፍሪካ አወዛጋቢ ከሆኑ የሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑ በብዙ ተመራማሪዎች ይጠቀሳል። የአስዋን ግድብ የግንባታ ሂደትም የአንድ ወገን እርምጃና የጥፋት አሻራ የተስተዋለበት ነው ብለዋል።
ግብፅ የአስዋን ከፍተኛ ግድብ ስትገነባ፣ የተፋሰሱን ሀገራት በተለይም የናይል ውሃ ዋና ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን በፍጹም አለማማከሯን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ በወቅቱ በይፋ ተቃውሞዋን ብታቀርብም፣ የግብፅ መንግስት ተቃውሞዋን ወደ ጎን በመግፋት ግድቡ ያለ ኢትዮጵያ ፈቃድና ስምምነት መገንባቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አስታውሰዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የግድቡ መገንባት ከ100 ሺህ በላይ የኑቢያ ማህበረሰብ አባላትን ከመሬታቸውና ከጥንታዊ መኖሪያቸው በማፈናቀል የማህበረሰብና የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉን ጠቅሰዋል።
በአሜሪካ እና በብሪታንያ በወቅቱ የተመዘገቡ ሰነዶች፣ በአስዋን ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ከዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ሰፊ ምክክር ባለመደረጉ የነበረውን ስጋት በግልጽ ያመላከቱ መሆናቸውንም ነው ያስታወሱት።
ከ1952 እስከ 1960 ባሉት ጊዜያት የተመዘገቡ 15 ይፋዊ መዝገቦች ይህንን ስጋት አስፍረዋል ብለዋል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ የገነባችው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እ.ኤ.አ. በ2015 በተፈረመው የመርሆች መግለጫ ስምምነት መሠረት ዘመናዊ የሕግ ማዕቀፍን በመከተል የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ግብፅ ኢትዮጵያን ከመንቀፏ በፊት፣ አስዋን ግድብን ያለ ኢትዮጵያ ስምምነት ለምን እንደገነባች እና ከ100 ሺህ በላይ ኑቢያውያንን ለምን እንዳፈናቀለች በግልጽ ማስረዳት እንዳለባት አብራርተዋል።
ግብፅ የአስዋን ግድብን ከየትኛውም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ምክክር ሳታደርግ መገንባቷ፤ እንዲሁም የጉዳት ጥናት እንኳ ሳይደረግ ኑቢያውያንን ከኑራቸውና ከቀያቸው በማፈናቀል ለከፍተኛ ችግር በመዳረጓ ግድቡ የጥፋት ውርስ ነው ብለውታል።
ኢትዮጵያ በወቅቱ ምክክር እንዲደረግ ያቀረበችው ተደጋጋሚ ጥያቄም በግብፅ በኩል መልስ አላማግኘቱን የጠቀሱት ሚንስትሩ፣ በተቃራኒው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ እ.ኤ.አ. በ2015 በተፈረመው የመርሆች ስምምነት መሰረት ለውይይት ተደራሽ መደረጉን ገልፀዋል።
ከዚህ አኳያ ግብፅ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ኢትዮጵያን ለመንቀፍ ምንም አይነት ሞራላዊና ምክንያታዊ መሠረት እንደሌላት ነው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አፅንኦት የሰጡት።
በታደሰ ሽፈራው