AMN- ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራሮችና ሠራተኞች የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ በየካ ተራራ የችግኝ ተከላ በማከናወን አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ተቋሙ በየዓመቱ በአካባቢ ጥበቃ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ባህሉን በመቀጠል፣ ዘንድሮም በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

በመርሐ ግብሩም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ፣ የተቋሙ ሠራተኞች የዜናና የፕሮግራም ሽፋን ከመስጠት ባለፈ፣ በተለያዩ ሀገራዊ የልማት ሥራዎችና በሰው ተኮር በጎ አድራጎቶች በግንባር ቀደምትነት ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።

ቀደም ሲል በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የተተከሉ ችግኞችን በበጋ ወራት ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ ከፍተኛ የጽድቀት መጠን ማስመዝገባቸውን ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ አሁንም በየካ ተራራ የተተከሉትን ችግኞች በመከታተል ረገድ አርአያነታቸውን እንደሚያስቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ተቋሙ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉት ችግኞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በዜና እና በፕሮግራም በመከታተል ዘገባ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ሚዲያው የከተማዋን የ24/7 ንቁ የሥራ ባህል መመሪያ በማድረግ፣ ያለ እረፍት መረጃ የማቅረብና ለከተማዋ አረንጓዴ ሽፋን እድገት የበኩሉን የማበርከት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚወጣም አመልክተዋል።
በወርቅነህ አቢዮ