AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የውይይት ባህልን ለመገንባት ትልቅ መሰረት መጣሉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ተመካካሪዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በስምምነት፣ በጥቂቶቹ ላይ ደግሞ የልዩነት አስተያየቶችን ባካተተ መልኩ በብዙዎቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል።
በሂደቱ ሁሉም የምክክር መድረኮች በመደማመጥ፣ በመከባበር እና በመቻቻል የተቃኙ እንደነበሩ ያረጋገጡት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማም ልዩነት ያላቸው አካላት ተወያይተው የጋራ መግባባት በመፍጠር በጋራ ወደፊት እንዲራመዱ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክር “አሸናፊና ተሸናፊ የሚለይበት ወይም አንዱ ወገን ተሸንፎ ሌላው የሚያሸንፍበት ውድድር አይደለም” ያሉት ኮሚሽነሯ፣ በሂደቱ ተመካካሪዎች እርስ በእርስ በመቀራረብና የተለያዩ አመለካከቶችን በማዳመጥ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ያሉባትን የሀሳብ ልዩነቶች በውይይት ለመፍታት ያሳየችበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለምክክር ጉባኤው መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትና ለአካታችነቱ ቁርጠኝነት ላሳዩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
በታምራት ቢሻው