አርሰናል ከ ኮቬንትሪ ሲቲ ፦ የውድድር ዓመቱ የመክፈቻ ጨዋታ

AMN- ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ2026/27 የውድድር ዘመን ዛሬ ይጀምራል።

ባለፈው የውድድር ዓመት 85 ነጥብ በመሰብሰብ የሊጉ አሸናፊ የሆነው አርሰናል የዋንጫ ክብሩን ለማስጠበቅ በሜዳው ኤምሬትስ ኮቬንትሪ ሲቲን በመግጠም ይጀምራል።

በርካቶች የዋንጫ አሸናፊ ቅድመ ግምታቸውን ሲሰጡ በቀዳሚነት ያስቀመጡት አርሰናል ነው። የሰሜን ለንደኑ ክለብ በጠንካራው የአማካይ ስብስቡ ላይ ብራዚላዊውን ቡርኖ ጉማይሬሽ ጨምሯል። የዊሊያም ሳሊባ ጉዳት ክፍተት እንዳይሆን ኢዝሪ ኮንሳ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ለንደን ደርሷል።

መድፈኞቹ ምናልባት የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ተጨማሪ ተጫዋች የሚያመጡበትም እድል አለ። ጠንካራ ስብስባቸው እንዲሁም የባለፈው የውድድር ዘመን የዋንጫ አሸናፊ መሆናቸው ተዳምሮ ለተከታታይ የዋንጫ ድል ታጭተዋል።

ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ ይልቅ ጥንቅቅ ያለ የሚመስለው አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ በቀላሉ ሦስት ነጥብ የሚያሳካበት እንደሚሆን ተገምቷል። የሚኬል አርቴታው ቡድን በ2021/22 በብሬንት ፎርድ ከተሸነፈ በኋላ በተከታታይ ባደረጋቸው አራት የውድድር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታዎችን በሙሉ አሸንፏል።

ዛሬ ቡድኑ ድል ከቀናው ሚኬል አርቴታ በትንሽ ጨዋታዎች 150 የፕሪምየር ሊግ ድል ያሳካ አምስተኛው አሰልጣኝ ይሆናል። አርቴታ ከ247 ጨዋታዎች 149 ድል አስመዝግቧል። ፔፕ ጋርዲዮላ ፣ ጆዜ ሞሪንሆ ፣ የርገን ክሎፕ እና ሰር አሌክስ ፈርጉሰን 250 ባልሞላ ጨዋታ 150 ድል ያስመዘገቡ አሰልጣኞች ናቸው።

የአርሰናል ተጋጣሚ ኮቬንትሪ ሲቲ ቻምፒየንሺፑን በበላይነት በማጠናቀቅ ነው ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገው። በቀድሞ የቼልሲ ታሪካዊ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ የሚመራው ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ከ25 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ፍራክ ላምፓርድ በተጫዋችነትም በተቃራኒ የገጠመው ሚኬል አርቴታን በአሰልጣኝነት ስድስት ጊዜ ገጥሞ አንዱን ብቻ አሸንፏል። አርቴታ በበኩሉ የአራቱ ጨዋታ አሸናፊ ሆኗል።

ዛሬስ ምን ዓይነት ውጤት ይመዘገባል? ምሽት 4:00 በኤምሬትስ የሚከናወነው ጨዋታ ምላሽ ይሰጠናል።

በጨዋታው በአርሰናል በኩል ዊሊያም ሳሊባ እና ዩሪየን ቲምበር አይሳተፉም። አጥቂው ቪክቶር ዮኬሬሽ ከተጫወተ የቀድሞ ክለቡን የሚገጥም ይሆናል። ስዊድናዊው አጥቂ ስፖርቲንግ ሊዝበንን ከመቀላቀሉ በፊት በኮቬንትሪ ሲቲ ጥሩ ጊዜ አሳልፎ ነበር።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review