AMN – ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዘመናት የፖለቲካ ቁርሾዎቿን እና አውዳሚ የደም አዙሪትን በመስበር፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደት አዲስ የዲሞክራሲ እና የሰላም ምዕራፍ መክፈቷ በትናንትናው ዕለት በታላቅ ብሔራዊ ኩራት ተበስሯል።
ባለፉት 4 ዓመታት የዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ አልፎ ከ4 ሺህ በላይ ወኪሎችን በማሳተፍ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለ46 ቀናት የተካሄደው ይህ ታሪካዊ ጉባኤ የሀገረ-መንግሥት ታሪካዊ ተቃርኖዎች በአፈሙዝ ኃይል ለመፍታት ሲደረጉ ከኖሩ አውዳሚ የጦርነት ልማዶች አላቆ በምክክር የፀናች ኅብረ-ብሔራዊት ሀገር ማጽናት የሚያስችል በር ከፍቷል።
በጉባኤው እንደ ሀገር የተለዩ ግዙፍና አበይት አጀንዳዎች በሰለጠነ መንገድ ተመክሮባቸው ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል!
ይህ ታሪካዊ የምክክር ጉበኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርአያነት የሚጠቀስ የሰላም ሰነድ ሆኗል ። ኢትዮጵያንም ከነባሩ የ’አሸናፊ-ተሸናፊ’ የተሰበረ የፖለቲካ ትርክት አሻግሯታል።
ለመጀመሪያ ገዜም ሁሉም ድምጾች የተሰሙበት እና የጋራ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት የአብሮነት ውል እንድትሳር አድርጓታል ። ከዚህ በኋላ የትኛውም ቡድን ወይም ኃይል ለግጭት እና ለአመፅ ማስተንፈሻ ‘የውይይት መድረክ አጣሁ’ የሚል አሳማኝ ምክንያት ሊኖረው እንደማይችል በተግባር ተረጋግጧል።
ይህ የምክክር ሂደት የትውልዳችን አዲስ መንገድ ሆኖ በማገልገል፣ ያለፉት ትውልዶች በጽኑ ተመኝተውት ያላዩትን በምክክር የጸና አብሮነት አረጋግጧል። በአኅጉራዊ እና ጂኦፖለቲካዊ አውድም፣ አፍሪካ የራሷን ችግሮች በራሷ ጥበብ መፍታት የምትችልበትን አቅም በዓለም ፊት ያስመሰከረ የሰላም ሞዴል መሆን ችሏል።
መንግሥት ከዚህ ሂደት ሕዝባችን የሚገኘውን የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ፋይዳ በመገንዘብ፣ ሂደቱን በሙሉ ቁርጠኝነት ሲያግዝ ቆይቷል በቀጣይም የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደረጋል ። ሀገር የምትገነባውና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጸናው በፖለቲካ ውል ብቻ ሳይሆን፣ በጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር እና የጋራ መከባበር ባህል ነው።
በቀጣይም የፖለቲካ አውዱ ከነፍጥ ኃይል ሙሉ በሙሉ ወጥቶ በይቅርታ እና በሐሳብ ልዕልና እንዲመሠረት እና በምክክር የተከፈተው በር ዘላቂ የሰላም ማዕቀፍ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉንም አቅሞች አስተባብሮ ለዓላማው መጠቀም ከሁላችንም ይጠበቃል።
እየተመካከርን ሀገር እንገነባለን፤ ሀገር እየገነባንም እንማከራለን’ጥላቻን ለልጆቻችን አናወርስም ፤ በሰለጠነ የምክክር መንገድ እና በተጋመደ አብሮነት የበለጸገች እና ሉዓላዊ እናኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት