ጠንካራ ሀገር መገንቢያው ሥልጡን መንገድ – ምክክር

AMN- ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያውያን መስተካከል አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ላይ በራሳቸው አስተባባሪነትና መሪነት፤ የመረጧቸውን አጀንዳዎች መሠረት በማድረግ ጠንካራ የጋራ ሀገርን ሊገነባ በሚችል የሰለጠነ መንገድ መክረው በስኬት አጠናቀዋል፡፡

እንዲህ ያለው ልዩነትን በምክክር የመፍታት ልምምድ ከዜጎች አልፎ ለቀጣናውም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው፡፡

ግጭትና ጦርነት ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ የተገነዘቡና ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 4 ሺህ ተመካካሪዎች የግል ጉዳዮቻቸውን ወደ ጎን በመተው በመዲናችን አዲስ አበባ በተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ በንቃት ተሳትፈዋል፤ ለጋራ ሀገር የሚበጀውን የውሳኔ ሐሳብም አቅርበዋል፡፡

አካታች በሆነው በዚህ የምክክር ጉባዔ ላይ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ የተወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

ተወካዮቹ በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ባደረጉት ሁሉን አቀፍ ውይይት የ130 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ድምፅ አንጸባርቀዋል፡፡

ላለፉት 46 ቀናት በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ የቆዩት ተመካካሪዎች ኢትዮጵያውያን መተሳሰብ፣ አብሮነት፣ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ለማዳመጥና ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንን እንዲሁም መከባበርን አጉልተው ያሳዩበት ነው፡፡

ተመካካሪዎች አንዱ የሌላውን ሀሳብ በማክበርና በማዳመጥ እንዲሁም “የእርሱ ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው” በማለት ኢትዮጵያ በምክክር እንድትጸና እና እንድታሸንፍ አድርገዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የምትገነባው በዚህ የሰለጠነ መንገድ ብቻ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን ለቀጣናው ሀገራትም ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡

በጉባዔው የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፤ ጉባኤው ከተነጋገርን የማንፈታው ሀገራዊ ችግር እንደሌለ በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡

መመካከር ለጋራ መግባባት መሠረት በመሆን ሰላምን እንደሚያመጣ እና የተለያዩ ሀሳቦችን በማቀራረብ አንድ የማድረግ አቅም እንዳለው አመላክተዋል፡፡

ታሪካዊ ስብራቶችን ለመጠገን፣ አለመግባባቶችን በውይይት ፈትቶ ጠንካራ ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር እንዲሁም የታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ክብር ከፍ ለማድረግ የምክክር ሂደቱ የላቀ ፋይዳ አለው፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ምክክሩ ስኬታማ እንዳይሆን ሐሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች በማሰራጭት ውዝግብ ለመፍጠር ቢሞክሩም የምክክር ኮሚሽኑ ተቋማዊ ገለልተኛነቱን በመጠበቅና ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆኑን በተግባር በማረጋገጥ ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review