አፍሪካውያን በራስ አቅም የጤና ሉዓላዊነታችንን ልናረጋግጥ ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – ነሐሴ 15/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ 13ኛውን የምሥራቅ አፍሪካ ጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በይፋ ከፍተናል ብለዋል።

ከ130 ዓመታት በፊት ቀደምት ኢትዮጵያውያን በዓድዋ በአይበገሬነት ያስመዘገቡት ድል፣ ዛሬ የሕዝባችንን ጤና በራስ አቅም የመጠበቅ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ መደገም አለበት ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የጤና ሉዓላዊነት ማለት መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን በራሳችን የማምረት፣ የጤና ባለሙያዎቻችንን የማሰልጠንና የማቆየት፣ እንዲሁም ወረርሽኞችን ወይም የጤና ቀውሶችን የዓለምን እጅ ሳንጠብቅ በራሳችን የመቋቋም ብቃት መፍጠር ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን አፍሪካዊ ዓላማ ለማሳካት የመድኃኒት፣ የመመርመሪያ ቁሳቁሶችና የሕክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረትን እያጠናከረች ትገኛለች።

አዲስ አበባን አፍሪካውያን ጥራት ያለው እና የላቀ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙባት የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ ሆስፒታሎችንና የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ናት።

መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ አቅሞችን በመጠቀም የማይበገር የጤና ሥርዓት መገንባቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።

በመጨረሻም ክምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጤናው ዘርፍ የግል ባለሀብቶች ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው የሚሠሩበት አህጉራዊ መድረክ እንዲኖር፣ የአፍሪካ ጤና ጥበቃ ፌዴሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲመሠረት መንግሥታችን ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review