AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም.
ዶክተር ሳውዳ ሲራጅ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ቶሎ ያልታከመ የጥርስ ሕመም በጤና ላይ ሊያስከትላቸው ስለሚችሉ ከባድ ጉዳዮች እና መፍትሄዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቶሎ ያልታከመ የጥርስ ሕመም የሚያስከትላቸው ዋና ዋና አደጋዎች፡-
የቆየ የጥርስ ኢንፌክሽን ከሙሌት እና ከስር ሕክምና አልፎ ጥርሱ እንዲነቀል ያደርጋል።
አንድ ጥርስ ሲነቀልና ወዲያውኑ ካልተተካ፣ አጎራባች ጥርሶች ቦታቸውን ሊስቱ፣ ሊሸረሸሩና ሊጎዱ ይችላሉ።
ኢንፌክሽኑ ረጅም ጊዜ ሲቆይ እየሰፋ በመሄድ የመተንፈሻ ቱቦ አካላትን እስከ መዘጋትና እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል አደገኛ እብጠት ሊፈጥር ይችላል።

በጊዜ ያልታከመ የጥርስ ኢንፌክሽን ወደ ተለያዩ የልብ ሕመሞች (በተለይም ኢንፌክቲቭ ኢንዶካርዳይትስ) ሊያጋልጥ ይችላል።
በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ እና የመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የሚከሰት የጥርስ ሕመም ለማከም እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ፣ ለእናቲቱም ሆነ ለፅንሱ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ችግሩ ሲባባስ የሚደረጉ ሕክምናዎች፣ የጥርስ መተኪያ አርቲፊሻል ጥርሶች እና የሚያስፈልጉ እቃዎች ውድ ስለሆኑ ከፍተኛ ወጪን ያስከትላል።
የጥርስ ጤንነትን ለመጠበቅ የሚረዱ የመፍትሄ ሃሳቦች፡-

በጊዜ መታከም፡ ጥርስን በጊዜ ሲታከሙ ሕክምናው ከመነቀል ይልቅ በቀላል ሙሌት ወይም በስር ሕክምና ሊስተካከል ይችላል።
ንጽህናን መጠበቅና ምግብ መምረጥ፡ ጣፋጭ ምግቦችን መቀነስ፣ አዘውትሮ የጥርስ ንጽህናን መጠበቅ እና መደበኛ የጥርስ ምርመራ ማድረግ ተፈጥሯዊ ጥርስ ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም ያስችላል።
ከተፈጥሮ ጥርስ ጋር ምንም አይተካከለም የሚሉት ዶክተር ሳውዳ፣ አርቲፊሻል ጥርስ ቢተካም እንደ ተፈጥሯዊው ጥርስ ሊሆን ስለማይችል፣ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ከሁሉ በላይ ይመከራል።
የተፈጥሮ ጥርሳችንን ለብዙ ዓመታት ለመጠቀም እና ከከፍተኛ የጤና እክልና የገንዘብ ወጪ ለመዳን፣ ጥርስን በጊዜ የመታከም ልምድ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ