AMN-ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን ተከተሎ፣ የኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) ልዩ ቦርዲንግ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ጃላል ግርማ ኩሳ 591.6 በማስመዝገብ በሀገር አቀፍ ደረጃ 1ኛ በመውጣት ድንቅ ታሪክ ሰርቷል።
የጃላል ግርማ ኩሳ አባት አቶ ግርማ ኩሳ የልጃቸውን የስኬት ሚስጥር ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል አጋርተዋል፡፡
በዚህም ልጃቸው ስኬት በእድል ሳይሆን በጠንካራ የንባብ ባህልና የተረጋጋ ስብዕና የተገኘ መሆኑን ስረድተዋል።
አቶ ግርማ ኩሳ፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ የቤተሰብን ምክር መቀበልና ምቹ በሆነ የትምህርት አካባቢ መማር ለተማሪ ጃላል ውጤት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ጃላል፤ አብዛኛውን ጊዜውን በንባብ እንደሚያሳልፍና ከማህበራዊ ሚዲያ ፍጹም የራቀ መሆኑን አባቱ ግርማ ኩሳ ተናግረዋል፡፡
“ጃላል የቤተሰቡን ምክር ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ጥሩ ስነ-ምግባር ያለውና ታዛዥ ልጅ ነው” ያሉት አቶ ግርማ፤ የልጃቸው ስኬት በእድል ብቻ የተገኘ ሳይሆን ጠንካራ የንባብ ባህልና የተረጋጋ ስብዕናው ያመጣው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጃላል የትምህርት ጉዞ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ስኬታማ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጃርሶ ከተማ እንዲሁም ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በዚሁ ዞን ጊምቢ ከተማ ትምህርቱን ሲከታተል በሁሉም የትምህርት ደረጃዎቹ አንደኛ በመውጣት ነው ያጠናቀቀው፡፡
ይህንን የልህቀት ጉዞውንም በኦልማ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በመቀጠል በብሔራዊ ፈተናው የሀገሪቱ ከፍተኛ ነጥብ አስመዝጋቢ ሊሆን ችሏል፡፡
የልጃቸውን አስደሳች የፈተና ውጤት መጀመሪያ ከቤተሰብ መስማታቸውን የገለጹት አቶ ግርማ፤ ለውጤቱ የቤተሰብ ምክርና የልጁ ጥረት ከፍተኛውን ድርሻ ቢወስድም የኦሮሚያ ልማት ማህበር ተማሪዎች በጥሩ ሁኔታ እንዲማሩ የፈጠረው ምቹ ሁኔታና ያደረገው ድጋፍ ጉልህ ሚና እንደነበረው ጠቁመዋል፡፡
የተማሪ ጃላል ግርማ ታሪክ፤ ትልቅ ውጤት በአንድ ጀንበር የሚመጣ ሳይሆን ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም፣ በንባብ በመጽናት፣ ከማዘናጊያ ነገሮች በመራቅና የተገኘውን የትምህርት እድል ወደ ላቀ ደረጃ በመቀየር የሚገኝ መሆኑን ያስተምራል፡፡
ኤ ኤም ኤን ለትምህርት ኮከቡ ጃላል ግርማ ኩሳ ወደፊት ለሚጠብቀው የከፍተኛ ትምህርት ህይወቱ መልካም እድልን ይመኛል።
በደራርቱ ተሬሳ