ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቶቿን የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መንገድ ማልማቷን አጠናክራ መቀጠል አለባት

AMN – ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቶቿን የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራትና ጎረቤቶቿን በማይጎዳ መንገድ ማልማቷን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት የውሃ ሀብት ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል።

ግብፅ በዓባይ ወንዝ ምንም ዓይነት የውሃ ምንጭ አበርክቶ ሳይኖራት በኢትዮጵያ ላይ የምታቀርበው መሠረተ ቢስ ክስ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ነው የገለጹት።

የውሃ ሃብት ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታራምደው የሺህ ዘመናት ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም ግትር አቋም ከራስ ወዳድነት የሚመነጭ ስሁት ትርክት ነው ብለውታል።

የሕዳሴ ግድብም የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትን የደለል ክምችት፣ የጎርፍና የድርቅ አደጋ በመቀነስ እንዲሁም የሀገር ውስጥና ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ትስስርን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ በረከት እያስገኘ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የግብፅ የፖለቲካ ልሂቃን በቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች በመቸንከር ዓባይን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎትና ሕዳሴ ግድብ ላይ ስሁት ትርክታቸውን በመንዛት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም ሕዝቦቿን በማስተባበር በዓለም አቀፍ ሕግና መርህ በሳይንሳዊ መንገድ ሕዳሴ ግድብን በመገንባት ፍትሐዊ የድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብት ተጠቃሚነትን በተግባር ማስመስከሯን አስረድተዋል።

የተፋሰሱን ሀገራት የዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት ድርድርና ስምምነቶች በማስተጓጎልም የተሳሳተ አማራጭን እየተከተለች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም የውኃ ሀብቶቿን የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራትና ጎረቤቶቿን በማይጎዳ መንገድ ማልማቷን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አስገንዝበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ሕዳሴ ግድብና ሌሎች የኃይል ማመንጫ ግድቦች የኢትዮጵያን የውኃ ልማት ዕውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯል ብለዋል።

በቀጣይም በዓለም አቀፍ ሕግና መርህ በመመስረት በዓባይና ሌሎች የውኃ ሀብቶች ላይ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ የልማት ሥራን ማስቀጠል እንዳለባት ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review