ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች የአዲስ አበባን የስማርት ሲቲ ጉዞ እያፋጠኑ ነው

AMN – ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከተማ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በመተግበር “ስማርት ሲቲ” የመሆን ግቧን እውን እያደረገች ትገኛለች፡፡

በተለይም በትራፊክ አያያዝ እና በከተማዋ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያመጡት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ስፍራዎች፣ የመዲናዋን ዘመናዊነት እና የዲጂታል ሽግግር በግልጽ የሚያሳዩ አበይት ማረጋገጫዎች ሆነዋል፡፡

በመዲናዋ የተገነቡት እነዚህ አዳዲስ የመኪና ማቆሚያዎች ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ የታገዙ ናቸው፡፡

አሽከርካሪዎች ቦታ ፍለጋ የሚያባክኑትን ጊዜ የሚያስቀሩ የሞባይል መተግበሪያዎች፣ አውቶማቲክ የክፍያ ሥርዓቶች እና ዘመናዊ የቦታ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ተሟልተውላቸዋል፡፡

ይህ አሠራር የሰውን ንክኪ በመቀነስ ፈጣን፣ ፍትሃዊ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለ ሲሆን ቀደም ሲል ይፈጠር የነበረውን የቦታ እጥረት በመቅረፍ የመዲናዋን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያቀላጠፈ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ዘመናዊ የሕንፃ ጥበብን የተከተሉት እነዚህ የፓርኪንግ ሕንፃዎች፣ የመንገድ ዳር የዘፈቀደ ተሽከርካሪ ማቆምን በመግታት የከተማዋን ውበትና ገጽታ የሚያድሱ ሆነዋል፡፡

የኤክትሪክ ቻርጂንግ የተሟላለት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ የተሽከርካሪዎችን የካርቦን ልቀት እና የነዳጅ ብክነት በመቀነስ ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ለዚህ አዎንታዊ ለውጥ የከተማ አስተዳደሩ ከግሉ ዘርፍ ጋር ያደረገው ጠንካራ አጋርነት እና የአሽከርካሪዎች ትብብር ከፍተኛ ሚና መጫወቱ ተገልጿል፡፡

በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ የትራፊክ አስተዳደር ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊ የማድረግ እና የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያዘምኑ እና የሚያቃልሉ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review