አዲስ መሶብ ከአገልግሎት ማስፋፋት ጎን ለጎን የነዋሪዎችን አመኔታ ለመገንባት እየሰራ ነው

You are currently viewing አዲስ መሶብ ከአገልግሎት ማስፋፋት ጎን ለጎን የነዋሪዎችን አመኔታ ለመገንባት እየሰራ ነው

AMN- ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የማዕከላቱን ቁጥር ከማስፋፋት ባሻገር የመዲናዋ ነዋሪዎች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሙሉ አመኔታ እና ዘላቂ እርካታ እንዲኖራቸው በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጡ 11 ቋሚ የመሶብ ማዕከላት ያሉ ሲሆን በ2019 በጀት ዓመት ቁጥራቸውን ወደ 20 ለማሳደግ ታቅዷል፡፡

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ደግሞ የማዕከላቱን ቁጥር እስከ 66 ለማድረስ የሚያስችል ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ከ150 በላይ የመንግስት አገልግሎቶች በማዕከሉ በዲጂታል መንገድ እየተሰጡ እንደሚገኙ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ተጨማሪ አዳዲስ አገልግሎቶችን ወደ ስርዓቱ ለማስገባት ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ተቋሙ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ገደማ ቢሆነውም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ቅርንጫፎቹን በማስፋፋት ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋት ችሏል፡፡

ይህም በመዲናዋ ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ክፍተቶችን እና ብልሹ አሰራሮችን በዘላቂነት በመቅረፍ ዜጎች ግልጽ፣ ዘመናዊ እና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

ኢንጂነር ደሳለኝ አክለውም፤ የተቋሙ ዋና ዓላማ የቅርንጫፎችን ቁጥር ማብዛት ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት በማሳደግ የነዋሪዎችን አመኔታ እና ዘላቂ እርካታ ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review