AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም
በቀጣይ የከተማዋን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማስቀጠል የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 በጀት አመት እና የቀጣይ አምስት አመታት እቅድ ውይይት አካሂዷል፡፡ መድረኩ በመዲናዋ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶችን መሰረት በማድረግ በቀጣይ አምስት ዓመታት የህዝብን አደራ ለመወጣት ያለመ ነው፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ለውጥ መመዝገቡን አንስተዋል፡፡ በቀጣይም የከተማዋን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማስቀጠል የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በከተማ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት ህዝቡን ያረካ መሆን መቻል አለበት ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ ከተማዋን ጽዱ፣ ውብ አረንጓዴና ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ የሥልጣኔ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው በመግለጽ የበለጸገች ከተማ በምቹ መሰረተ ልማት፣ በተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ እና ንጹህ ጎዳናዎቿ ትገለጻለች ብለዋል፡፡
መሰረተ ልማቶችን መስራት ብቻ ሳይሆን ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሻገሩ ማድረግ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የሻምበል ምህረት