ተመድ የአፍሪካን ትክክለኛ ስፋት የሚያሳይ አዲስ የዓለም ካርታ አጸደቀ

You are currently viewing ተመድ የአፍሪካን ትክክለኛ ስፋት የሚያሳይ አዲስ የዓለም ካርታ አጸደቀ

AMN ነሐሴ 29/2018

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ፤ የአፍሪካን እውነተኛና ትክክለኛ መልክዓ-ምድራዊ ስፋት የሚያሳይ አዲስ የዓለም ካርታ በይፋ አጽድቋል።

ይህ ታሪካዊ ውሳኔ የተላለፈው በአፍሪካ ህብረት ስም በቶጎ አቅራቢነት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ሲሆን፣ ዓላማውም ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተዘጋጀውን የተዛባ የካርታ አሰራር እንዲያከትም ማድረግ ነው።

በውሳኔው መሠረት፣ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ላይ የዋለውና ለአፍሪካ አህጉር ትክክለኛ ያልሆነ ስፋት ይሰጥ የነበረው የሜርካቶር ካርታ ከስራ ውጪ እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል።

በምትኩ ደግሞ እንደ እ.ኤ.አ. በ2018 ይፋ የሆነውና የምድርን ትክክለኛ መጠንና ድርሻ የሚያንጸባርቀው “ኢኩዋል አርዝ”(Equal Earth) የመሳሰሉ ዘመናዊ እና እኩል አቀራረብ ያላቸው የካርታ ቀመሮች በስራ ላይ ይውላሉ።

ይህ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ 164 ሀገራት የውሳኔ ሀሳቡ እንዲፀድቅ ድጋፍ ሰጥተዋል።

የተለመደውና የድሮው ካርታ የተሰራው እ.አ.አ በ1569 በደች (ፍሌሚሽ) ካርታ ሰሪ በጄራርዱስ ሜርካቶር ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም በወቅቱ ለባህር ዳር መርከበኞች ማሰሻነት እንዲያገለግል ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ካርታ ከምድር ወገብ (Equator) እየራቀ ሲኬድ የመሬትን ስፋት እያጋነነ የሚያሳይ በመሆኑ፣ የምድር ወገብ አቅራቢያ የሚገኙ አካባቢዎችን በዕይታ በእጅጉ እንዲቀንሱ አድርጓል።

በዚህ የተዛባ የካርታ አሰራር ምክንያት አፍሪካ ከግሪንላንድ ደሴት ጋር ተቀራራቢ መጠን እንዳላት ሆና ስትታይ ቆይታለች።

አፍሪካ ከግሪንላንድ በ14 እጥፍ የምትበልጥ ትልቅ አህጉር መሆኗ ይታወቃል።

የዘመቻው ደጋፊዎች እና የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኞች ይህንን እርምጃ በዓለም አቀፍ የትምህርት ስርዓት እና የካርታ ስራ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀውን የምዕራባውያን አድሎአዊ እይታ ለማስተካከል የተወሰደ ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ አድርገው እንደወሰዱት ቢቢሲን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review