አዲስ አበባ ባለፉት አምስት ዓመታት በመንገድ መሠረተ ልማት ተጨባጭ የማንሰራራት ለውጦችን አሳይታለች

AMN -ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ጳጉሜን 2ን “የማንሰራራት ቀን” በማስመልከት በከተማዋ በመንገድ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችና መሠረተ ልማቶችን የሚያሳይ የፎቶ አውደ-ርዕይ አዘጋጅቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ራሻድ እንደገለጹት፤ አውደ-ርዕዩ በከተማዋ ባለፉት አምስት ዓመታት የተሰሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችን ለሕዝብ ለማሳየት ያለመ ነው።

ከተማዋ ባለፉት ዓመታት የሞተር አልባ ትራንስፖርት ማበረታቻ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን፣ የብዝሀ-ትራንስፖርቱን ለማሳለጥ የሚረዱ የመንገድ ማስፋፊያዎችንና አዲስ ግንባታዎችን ማከናወኗ ተገልጿል።

በተጨማሪም ምቹ የመኪና ማቆሚያዎች፣ ተርሚናሎች እና የዋሻ ውስጥ መንገድን ጨምሮ የተለያዩ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች መገንባታቸው ከተማዋ በዘርፉ አበረታች የማንሰራራት ሂደት ላይ መሆኗን እንደሚያመላክቱ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በዕለቱ በተዘጋጀው የፎቶ አውደ-ርዕይ ላይ አዲስ የተሰሩና የታደሱ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ማሳለጫዎች፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲሁም ባለሥልጣኑ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያከናወናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ለዕይታ ቀርበዋል።

በአውደ-ርዕዩ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

በቤተልሔም አየነው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review