AMN – ጳጉሜን 2/2018 ዓ.ም

የአርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ በአምቦ ከተማ እንደሚፈጸም ተገለጸ።
የአርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የአስከሬን አሸኛኘት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት አስፈጻሚ ኮሚቴ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠዉ መግለጫ የአርቲስቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ በአምቦ ከተማ በክብር እንደሚፈጸም አስታዉቋል።

የኮሚቴዉ ሰብሳቢ አቶ ለሚ ቤኛ እንደገለጹት ጳጉሜን 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳዉ 11:00 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለአርቲስቷ አስከሬን የክብር አሸኛኘት ይደረጋል።

የአርቲስቷ አስከሬን ከማለዳዉ 11:00 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ ኮሪያ ሆስፒታል ወደ መኖሪያ ቤታቸዉ አሸኛኘት ይደረግለታል።
በመኖሪያ ቤታቸዉ አሸኛኘት ከተደረገላቸዉ በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች፣ ወዳጅ ዘመዶቿ፣ አርቲስቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ለጀግናዋ አርቲስት አስከሬን የክብር አሸኛኘት ይደረግላቸዋል።

አርቲስቶችን በመወከል መግለጫዉን የሠጠዉ አርቲስት ኢቲቃ ተፈሪ በበኩሉ:- አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ በህይወት ዘመናቸዉ ትዉልድ ለመቅረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የኦሮሞ አርቲስቶች ተምሳሌት መሆናቸዉን ተናግሯል።
አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ በትግል ህይወታቸዉ በአምቦ ማረሚያ ቤት እስርና ከፍተኛ እንግልት የደረሰባቸዉ መሆኑንም ጨምሮ አስታዉሷል።
አርቲስቷ በህይወት በነበሩበት ወቅት ስሞት ሥርዓተ ቀብሬ በአምቦ ከተማ ይፈጸምልኝ ብለዉ መልዕክት ባስተላለፉት መሠረት ኮሚቴዉ ቃላቸዉን በማክበር ሥርዓተ ቀብራቸዉ በአምቦ ከተማ እንደሚፈጸም መወሰኑንም አርቲስት ኢቲቃ ተፈሪ ጨምሮ ገልጿል።
በወንድማገኝ አሰፋ