AMN – ጳጉሜን 3/2018
በጽናት በተገነባ አንድነትና ትብብር የሀገርን ሉዓላዊነትና የልማት ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ጳጉሜን 3 የጽናት ቀንን “አብሮነታችን ለጽናታችን፣ ጽናታችን ለዘላቂ ሉዓላዊነታችን” በሚል መርህ ሐሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል።
መርሃ ግብሩ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላት፣ የከተማዋ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች በተሳተፉበት ተከብሯል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የጽናት ቀን በተለያዩ ወቅቶች የገጠሙ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ የማይበገር ሀገራዊ ድልን ለማስመዝገብ ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚታደስበት ቀን ነው።
በጽኑ ዓላማ የተመራ ሠራዊት የውስጥና የውጭ ፈተናዎች የማያሸንፉት ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ሀገርን በመገንባት ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ የሚችል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በጽናት እና በአብሮነት በመቆም የውጭ ወራሪዎችን በመመከት የሀገርን ነጻነት ማስጠበቃቸውን አውስተው፤ የዛሬው ትውልድም በጽናት በመቆም ታላላቅ ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ መቻሉ የጽናቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የኢትዮጵያውያን የጽናትና የቁርጠኝነት ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጽናት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር በበኩላቸው፤ የጽናት ቀን የጸጥታ ኃይሎች ለሀገርና ለሕዝብ እየከፈሉ ላለው መስዋዕትነት ድጋፍና አጋርነት መግለጽ የሚያስችል መድረክ ነው ብለዋል።
ጽናት የኢትዮጵያውያን የቆየ ሀገራዊ መለያ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት፣ የዕድገትና የብልፅግና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በኃይል፣ በግብርና፣ በመኖሪያ ቤትና በሌሎች የልማት ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የሀገራዊ ጽናትና ቁርጠኝነት ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ሥራዎች ከተማዋን በተለያዩ ዘርፎች እያሻሻሉ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሀብቶችና አመራሩ በትብብር የሚሠሩበት ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።