በመስከረም ለሚከበሩ በዓላት የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በቂ ዝግጅት ተደርጓል

AMN -ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም

ከፊታችን ለሚከበሩት የአዲስ ዓመት፣ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት የከተማዋን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ያለመስተጓጎል ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት አስታወቀ።

ጽ/ቤቱ መጪዎቹን የዘመን መለወጫ አዲስ ዓመት፣ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላትን አስመልክቶ በከተማዋ የተከናወኑ ማዘጋጃ ቤታዊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ለበዓላቱ የሚያስፈልጉ ሁሉም ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ስራ አስኪያጅና የአገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ ተፈራ ሞላ(ዶ/ር) አስታውቀዋል።

በበዓላት ወቅት በርካታ አገልግሎቶች በአንድ ላይ የሚፈለጉ መሆኑ ታውቆ፣ ላለፉት ሦስት ወራት ከማዕከል እስከ ወረዳ አጋዥ ዝግጅቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ለአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ተጠሪ የሆኑ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በመግለጫው የተገኙ ሲሆነ ፣ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በየተቋማቸው ለህዝብ በዓላት የተደረጉ አጠቃላይ ዝግጅቶች መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንም በበዓላቱ ወቅት የሚፈለገውን የውሃ አቅርቦት ያለመስተጓጎል ለማቅረብ እና ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉን በመግለጫው አስታውቋል።

በላይሁን ፍስሃ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review