AMN- ጳጉሜን 05/ 2018 ዓ.ም

ነገ ተስፋም ሕይወትም ነው። ተስፋ ሕይወትን ያለመልማል፡፡ ነገን ለትልቅ ነገር ማለም የወደፊት መዳረሻን ለማወቅ ያስችላል።
መንግሥት በአሮጌው እና በአዲሱ ዓመት መካከል እንደ መሸጋገሪያ የምታገለግለዋን የጳጉሜን ወር ቀናት ለሀገር አንድነት እና ብልፅግና በሚጠቅሙ ስያሜዎች ሰይሞ እያከበረ ይገኛል፡፡ በዚህም ጳጉሜን 5 “የነገ ቀን” ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ጳጉሜን 5ን ስናከብር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የነገውን ትውልድ ታሳቢ አድርገው የተከናወኑ ሁለገብ የልማት ሥራዎችን በመቃኘት እና ለቀጣይ የብልፅግና ጉዞ መሠረት ሊሆኑ በሚችሉ ተግባራት ላይ አበክሮ በማሰብ ጭምር ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት መዲናችን አዲስ አበባ እና ሀገራችን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል። “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ሀገሪቱን በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እያስቀጠሏት ይገኛሉ።
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ አገልግሎቶችን ከቢሮክራሲ ነፃ ለማድረግ እና ዜጎች እንግልት ሳይገጥማቸው በአንድ ስፍራ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስቻለውን “የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት” እውን አድርጓል።
የሀገሪቱን የዲጂታል ምህዳር ደህንነት ለማረጋገጥ እና የመንግስት መረጃዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ የሳይበር ሉዓላዊነትን የሚያስከብሩ ተቋማዊ አቅሞች ተገንብተዋል።

የነገውን ትውልድ በእውቀት እና በክህሎት ለመገንባት የሚያስችሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ተሠርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የ”5 ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ” መርሐ-ግብር ወጣቶች በኮዲንግ፣ በሶፍትዌር ልማት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አቅማቸውን እንዲገነቡ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ወጣቶች ዘንድ ሰፊ ተሳትፎ እየታየበት ያለው ይህ ስኬት፣ የነገው ትውልድ በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችል ትልቅ የዛሬ ትጋት ውጤት ነው።
የኮሪደር ልማት እና የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄዎች መዲናዋን ለነዋሪዎቿ እና ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ፣ ውብ እና ተስማሚ አድርገዋታል።
ጳጉሜን 5 የነገ ቀን መከበሩ የነገውን ትውልድ ታሳቢ አድርገው የተከናወኑትን እንደ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የኮሪደር ልማት እና የክህሎት ስራዎች እንደ እርሾ በመጠቀም፣ ቀጣይ ብልፅግናን ሊያረጋግጡ የሚያስችሉ ሌሎች ለነገው ትውልድ ተስፋ የሚሆኑ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የሚገባበት ነው።
በአስማረ መኮንን
See less