AMN-መስከረም 2/2019 ዓ.ም
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ ሲጀምር ያለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ አርሰናል ሰንደርላንድን የሚገጥምበት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ዘንድሮም አጀማመሩ የሰመረ ሆኗል። በሁሉም ውድድር አምስት ጨዋታ አከናውኖ ነጥብ አልጣለም።
አርሰናል ባለፈው ዓመትም ያሳየው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ዘንድሮም አብሮት አለ። ካከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው ግብ የተቆጠረበት። የሚኬል አርቴታው ቡድን በተቃራኒው ተጋጣሚዎቹ ላይ 10 ግቦችን አስመዝግቧል።
በፕሪምየር ሊጉ ሦስት ጨዋታ አድርጎ ሁሉንም ያሸነፈው አርሰናል ዛሬ ለአራተኛ ድል ይፎካከራል። ክለቡ በሊግ ውድድር ታሪኩ የመጀመሪያ አራት ጨዋታዎችን አሸንፎ የሚያውቀው በአምስት አጋጣሚዎች ነው። ከእነዚህ ውስጥ በሦስቱ የውድድር ዓመቱን በዋንጫ ሲያጠናቅቅ ፤ በሁለቱ ደግሞ 2ኛ ደረጃ ይዞ ጨርሷል።
ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ ተመልሶ የዩሮፓ ሊግ ተሳታፊ የሚያደርገው ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ሰንደርላንድ የዘንድሮ አጀማመሩ ወጥነት የጎደለው ሆኗል።
በቀድሞ የአርሰናል አማካይ ግራኒት ዣካ አምበልነት የሚመሩት ሰንደርላንዶች በሊጉ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፈው ፣ በአንዱ አቻ ተለያይተው ፣ በሌላኛው ተሸንፈው በአራት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በሁለቱ ክለቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት አርሰናል የበላይነቱን ይወስዳል። መድፈኞቹ ሰንደርላንድን በገጠሙባቸው 29 የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠማቸው በአንዱ ብቻ ነው። 18ቱን አሸንፈው በ10ሩ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
በስታዲየም ኦፍ ላይት የሚደረገው ጨዋታ ምሽት 4፡00 ላይ ይጀምራል። ዛሬ በሚከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች 11፡00 ላይ ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ሀል ሲቲን ያስተናግዳል ፤ በተመሳሳይ ሰዓት ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ፉልሃምን ይገጥማል።
አስቶንቪላ ከ ከኖቲንግሃም ፎረስት ፤ ቦርንማውዝ ከ ብሬንትፎርድ እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከ ኢፕስዊች ታውን በተመሳሳይ 11፡00 ላይ ጨዋታቸውን ይጀምራሉ። ምሽት 1፡30 አስከፊ አጀማማር ያደረገው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሜዳው ኤቨርተንን የሚያስተናግድበት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።
በሸዋንግዛው ግርማ