የእመርታ ቀንን አስመልክቶ ከተማ አቀፍ የብዙሃን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሄደ

You are currently viewing የእመርታ ቀንን አስመልክቶ ከተማ አቀፍ የብዙሃን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሄደ

AMN- ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

የጳጉሜን 1 የእመርታ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተማ አቀፍ የብዙሃን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

መርሐ ግብሩ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም ነዋሪዎች በተገኙበት ነው የተካሄደው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ ዳዊት ትርፉ፤ በከተማዋ ብሎም በኢትዮጵያ የስፖርት ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በርካታ ድሎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የተገኙት ሁለገብ እመርታዎች የጠንካራ ሥራ፣ የትብብር እና የራዕይ ውጤቶች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያን ብልጽግና በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በስፖርት ልማት ማዕቀፎች ውስጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ልመንህ ምረቱ በበኩላቸው፤ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ባስመዘገበው ተጨባጭ እመርታ ሀገሪቱ ከነበረችበት የተረጅነት ጥገኝነት ተላቃ በራስ አቅም የመቆም ብስራት ማብሰሯን ገልጸዋል።

ይህ የለውጥ ጉዞ የነዋሪውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው ማለታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት አበይት ስኬቶች የሴቶችን፣ የወጣቶችን እና የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያረጋገጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሴቶች ሊግ ም/ሰብሳቢ ፀደነያ ግርማይ ናቸው፡፡

ጳጉሜን 1 የእመርታ ቀንን ከሀገራዊ ድሎችና ስኬቶች ጋር በማቀናጀት ዜጎች በአካል ብቃትና በንቃት አዲሱን ዓመት እንዲቀበሉ የሚያስችል ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎችና ወጣቶችም፤ ቀኑን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማክበራቸው ለአዲሱ ዓመት አዲስ መንፈስና ጉልበት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች እና ዘመናዊ የስፖርት ማዕከላት መገንባታቸው ለወጣቶች ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ ተስፋ የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው አዲሱን ዓመት በድል አድራጊነት ስሜት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review